የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ ስለዋልያዎቹ አሠልጣኝ ሀሳብ አጋርተዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትነት እና የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ እንደሚከናወን ይታወቃል። ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ግለሰቦችም ከሰሞኑን ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫዎችን እየሰጡ የሚገኝ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራም ቀትር ላይ የሰጡትን መግለጫ ማቅረባችን ይታወቃል። ክቡር ፕሬዝዳንቱ የዋልያዎቹን አለቃ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ውል በተመለከተ የሰጡትን ሀሳብም እንደሚከተለው አቅርበናል።
“ከአሠልጣኙ ጋር በተገናኘ የሥራ-አስፈፃሚው በተሟላ ሁኔታ ስላልተሰበሰበ ነው መዘግየት የመጣው ፤ መንጠባጠቦች አሉ። በግልፅ ከአሠልጣኙ ጋር ተነጋግረናል። እኔ በፕሬዝዳንትነት ብቆይ አሠልጣኙ ይቀጥላል። አሁን ይሄንን ስል አሠልጣኙ የሚመርጡኝ እንዳይመስል ፤ ድምፅ ፍለጋ ነው እንዳይባል አሠልጣኙ አይመርጡኝም። ግን እኔ ብቆይ ይቀጥላሉ። ከምን አንፃር ከተባለ እያደረጉ ካሉት ሥራ ጋር ተያይዞ። አሁን የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ ላይ አንደኛ ደረጃ ላይ ናቸው። ብሔራዊ ቡድኑንም ተረክበው ለአፍሪካ ዋንጫ አሳልፈዋል። እዛ ሄደው ምን ውጤት አምጥተዋል የሚለው ሌላ ነው። ግን እስቲ ውድድሩን ቤታችን እናስተናግድ።
“በአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ 8 ዓመት ጠብቀን ተሳትፈን ለምን እዚህ ደርሰህ ተመለስክ ማለት አይገባም። በመድረሳችን የፌዴሬሽኑ የገንዘብ አቅም አበጥ ብሏል። ውድድሩ ላይ መድረስ ራሱ ጥቅም አለው። ከ54 ሀገራት የሀገራችን ባንዲራ ለ1 ወር ያህል ካሜሩን ስታዲየሞች ውስጥ ተውለብልቧል። ግብፅ ላይ ለተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እጣ ልናወጣ ስንሄድኮ ለአፍሪካ ዋንጫው ላለፉት ሀገራት ሲደረግ የነበረውን መስተንግዶ ያየ ይሸማቀቃል። ለአፍሪካ ዋንጫው ስታልፍ ክብሩ ራሱ ይጨምራል። የሀገር ስም ከፍ ይላል። ስለዚህ የሀገርን ስም ከፍ ያደረገ፣ ከ33 ዓመት በኋላን የግብፅ ብሔራዊ ቡድንን ያሸነፈን ቡድን ያሰለጠነን አሠልጣኝ ክብር መንፈግ ነው የሚሆንብን። እርግጥ ቆይቷል 6 ወር ቀድመን ማሳደስ ነበረብን ፤ ግን አሁንም የከፋ ነገር አይሰማም።”