አጥናፉ ዓለሙ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ በቅርቡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድሩን የሚጀምረው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመስከረም ወር የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ ውድድሩን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን በመግጠም የሚጀምር ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በአንድ ዓመት ውል ቀጥሯል። አሰልጣኙም ኃላፊነቱን ተረክበው ባለፉት ቀናት የተጫዋቾች ምልመላ እና ተዛማጅ ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበር ተጠቅሷል።

አሰልጣኝ አጥናፉ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፣ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው የሰሩ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን የማሰልጠን ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ናቸው።