ኢትዮጵያ ቡና ለ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከክለቡ የተመረጡ ተጫዋቾችን በፊፋ ህግ መሠረት ውድድሩ ሲቃረብ ብቻ እንደሚለቅ ገለፀ።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በትላንትናው ዕለት አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን ለዚህ ጨዋታም ለ35 ተጫዋቾች ጥሪን አቅርቦ ከቀጣዩ ሰኞ ነሀሴ 23 ጀምሮ ወደ ዝግጅት እንደሚገባ ይፋ ሆኖ ነበር። ለብሔራዊ ቡድኑ ከተጠሩ ተጫዋቾች መካከል ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ ጫላ ተሺታ ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ መሀመድ ኑርናስር እና ብሩክ በየነ የጥሪው አካል ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ በአንፃሩ ለተጫዋቾቹ የተደረገውን ጥሪን የተመለከተ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል፡፡
ክለቡ በደብዳቤው ለ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሶ “ተጫዋቾችን በአሁኑ ሰዓት መልቀቅ በአጠቃላይ የቡድኑ ዝግጅት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚያሳድር የጨዋታው ቀን ሲቃረብ በፊፋ መመሪያ መሠረት የተመረጡ ተጫዋቾችን እንደለቃለን፡፡” በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ ሰጥቷል።