“ተጫዋቾቼ ለመጫወት ስለተራቡ በጣም ደስተኛ ነኝ” ካርሎስ አሎስ ፌረር

የነገው የዋልያዎቹ ተጋጣሚ አሠልጣኝ ካርሎስ አሎስ ፌረር በጨዋታው ዋዜማ ስለቡድናቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ ለመካፈል በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ የ180 ደቂቃዎች ፍልሚያ ብቻ እንደሚቀረው ይታወቃል። ከሩዋንዳ ጋር ለሚደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታም አሠልጣኙ አዳማ ላይ መቀመጫቸውን በማድረግ ሲሰናዱ የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ወደሚያደርጉበት ታንዛኒያ አምርተዋል።

የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ባሳለፍነው እሁድ ተሰባስቦ የሁለት ቀናት የሀገር ቤት ልምምዱን ብቻ በማከናወን ትናንት ምሽት ኢትዮጵያ ተከትሎ ታንዛኒያ ገብቷል። በጨዋታው ዋዜማ ዛሬ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ቡድኑ ከማድረጉ በፊትም ስፔናዊው የ47 ዓመት አሠልጣኝ ካርሎስ አሎስ ፌረር ተከታዩን አጠር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

“ተጫዋቾቼ ለመጫወት በጣም ስለተራቡ በጣም ደስተኛ ነኝ። እርግጥ ከጠራኋቸው ተጫዋቾች ጋር ሰፋ ያለ የልምምድ ጊዜ አላሳለፍኩም ፤ አንድም የአቋም መፈተሻ ጨዋታም አላከናወንም። ግን ምንም ችግር የለውም። ጊዜው የምናለቅስበት አይደለም። ምንም ቢሆን ምንም ግን በተቻለ መጠን ጠንክረን መስራት አለብን።” ብለዋል።

ከአምስት ወራት በፊት የተቀጠሩት አሠልጣኙ ነገ ቡድኑን ከያዙ 3ኛ ይፋዊ ጨዋታቸው ሲሆን ወደ ታንዛኒያ ሲጓዙም 25 ተጫዋቾችን በመያዝ ነው።