ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ጋናዊ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል

ሀድያ ሆሳዕና የአጥቂ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆኑ ሁለት ጋናውያን ተጫዋቾችን በይፋ በዛሬው ዕለት ወደ ስብስብ ቀላቅሏል።

በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እየተመሩ እስካሁን የሰባት የሀገር ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሆነ የነባር ተጫዋቾችን ውል ያደሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አሁን ደግሞ በተደጋጋሚ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲነሳ የነበረውን አጥቂውን ሪችሞንድ ኦዶንጎን እና የአማካዩን ስቴፈን ናያርኮን በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ውስጥ በማስመጣት የክለቡ ንብረት አድርጓል፡፡

ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎ የዛምቢያውን ክለብ ቢውልድኮንን ከለቀቀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ በማለት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ደግሞ በግሉ በአዲስ አበባ ከተማ እጅግ ውጤታማ ጊዜያትን አሳልፎ አሁን ላይ ለሀዲያ ሆሳዕና መፈረሙ ተረጋግጧል።

ሌላኛው የሀድያ ሆሳዕና አዲሱ ተጫዋች የጋና ዜግነት ያለው የአማካይ ስፍራ ተሰላፊው ስቴፈን ኒያርኮ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን ጭምር ተጫውቶ ያሳለፈው አማካዩ ረዘም ያለው የእግር ኳስ ዘመኑን በሀገሩ በሚገኙት ዊ ኦል ስታር ፣ አሻንቲ ኮቶኮ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በአሻንቲ ጎልድ ቆይታን አድርጎ አሁን ላይ መዳረሻውን ነብሮቹን አድርጓል።

በሆሳዕናው አብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ከሳምንት በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መከወን የጀመረው ቡድኑ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ላይ አንድ የውጪ ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም በሂደት ላይ ስለመሆኑም ክለቡ በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል፡፡