ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ሾሟል

የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን በዋና አሰልጣኝነት ከቀጠሩ በኋላ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከአምስት ወራት በፊት ከተሾመው ረዳት አሰልጣኝ አለምሰገድ ወልደማርያም ውጪ ተጨማሪ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ቀጥሯል።

ሽመልስ አበበ በተጫዋቾችነት ያሳለፈበትን ክለብ በአሰልጣኝ ለማገልገል ተሹሟል፡፡ ሽመልስ በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ያሳለፈ እና 2007 ድሬዳዋ ከተማ ከታችኛው የሊግ ዕርከን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲመለስ በአምበልነት ቡድኑን ሲያገለግል የነበረ ሲሆን እግር ኳስን ካቆመ በኋላ ደግሞ ታዳጊዎችን በማሰልጠን እንዲሁም ድሬዳዋ ፓሊስን በአንደኛ ሊጉ በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግል ሰንብቶ የቀድሞው ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት ለማገልገል ተመልሷል፡፡

ሌላኛው ረዳት በመሆን የተሾመው የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሐመድ ጀማል ነው፡፡ የተጫዋችነት ዘመኑን በግብ ጠባቂነት በጅማ ፣ እርሻ ሰብል እና አዲስ አበባ ፓሊስ ውስጥ ያሳለፈው መሐመድ ላለፉት ስድስት ዓመታት የጅማ አባጅፋር የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን በርካታ ግብ ጠባቂዎች እንዲፈሩ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ በመቆየት የብርቱካናማዎቹ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ተቀጥሯል፡፡

በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን በጂም እና በሜዳ ተግባራት ላይ አተኩሮ እየሰራ የሚገኘው ክለቡ ለአንድ የውጪ ዜጋ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሙከራ ዕድልን የሰጠ ሲሆን ተጨማሪ ተጫዋች ከሀገር ውስጥ እንደማያካትት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ያጋሩ