በዋልያው ስብስብ የሚገኙት የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል

ከነገ በስትያ ከሱዳኑ አል-ሜሪክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ የሚገኙትን ተጫዋቾቻቸውን አግኝተዋል።

በአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገራችንን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር እንደሚወክል ይታወቃል። ቡድኑም ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር ላለበት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን በቢሾፍቱ ክቡር ይድነቃቸው አካዳሚ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውንም ወደ ታንዛኒያ በማምራት ከሲምባ ጋር አከናውኖ ነበር። ከነገ በስትያ ደግሞ ከሱዳኑ ክለብ አል-ሜሪክ ጋር ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዘ ዘግበን ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት ደግሞ ማክሰኞ ለሚደረገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታንዛኒያ የሚገኙትን የቡድኑን ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ አስመጥቷል። በዚህም በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ የሚገኙት ረመዳን የሱፍ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ሔኖክ አዱኛ፣ ምኞት ደበበ፣ ጋቶች ፓኖም እና ቸርነት ጉግሳ ዛሬ ረፋድ ከታንዛኒያ ወደ ኢትዮጵያ በረራ በማድረግ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ እንደገቡ አረጋግጠናል። ተጫዋቾቹም በአቋም መፈተሻው ጨዋታ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ከውል ማደስ ጋር ተያይዞ እስካሁን በፈረሰኞቹ መለያ መቆየቱ ያልተረጋገጠው አማኑኤል ገብረሚካኤል ግን እንዳልመጣ የዝግጅት ክፍላችን አረጋግጣለች።