የሩዋንዳ እና ኢትዮጵያን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

ኢትዮጵያ ግብፅን በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ስትረታ የጨዋታው የመሐል ዳኛ የነበሩት ቡሩንዲያዊ በሳምንቱ መጨረሻ በቻን የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመልስ መርሐ-ግብርም ሩዋንዳ እና ኢትዮጵያን እንዲመሩ ተመድበዋል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ ላይ ለመካፈል የአህጉሪቱ አባል ሀገራት በየቀጠናቸው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም በመጀመሪያው ዙር ሱዳንን በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፋ ከሩዋንዳ ጋር የተገናኘች ሲሆን የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዋንም ዳሬሰላም ላይ አከናውና 0ለ0 ተለያይታለች። ከቀናት በኋላ ነሐሴ 29 ደግሞ የመልሱን ጨዋታ ሩዋንዳ ላይ ታከናውናለች።

በሁዬ ስታዲየም የሚደረገውን ጨዋታ ደግሞ ቡሩንዲያዊ አልቢትሮች እንደሚመሩት ተረጋግጧል። ጋቶጋቶ ጆርጅ የጨዋታው የመሐል ዳኛ ሲሆን ሀቢማና ዊሊ እና ንዲሙንዚጎ ፓስካል የመስመር ረዳት እንዲሁም ንዱዊማና ጃፋሪ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል። የጨዋታው ኮሚሽነር የሆኑት ሳላ አህመድ መሐመድ ሳላ በበኩላቸው ከሱዳን እንደሆኑ ተመላክቷል።

የመሐል ዳኛው ጆርጅ ጋቶጋቶ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ግብፅን ከፍ ካለ የጨዋታ ብልጫ ጋር ስትረታ በተመሳሳይ የጨዋታው የመሐል ዳኛ እንደነበሩ አይዘነጋል።