ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ግልጋሎት እንድትሰጥ በፊፋ ጥሪ ተደርጎላታል፡፡
የዓለም ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ጨዋታ ውድድር ከጥቅምት 1 እስከ ጥቅምት 20 ድረስ በህንድ አስተናጋጅነት ይደረጋል፡፡ የውድድር የበላይ አካል የሆነው ፊፋ በዳኝነት የሚያገለግሉ ዳኞችን ከተለያዩ ሀገራት መምረጡንም ይፋ አድርጓል፡፡ አስራ አራት ዋና፣ ሀያ ስምንት ረዳት እና አስራ ስድስት የቪዲዮ ዳኞችን ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ ከአፍሪካ ሁለት የቪዲዮ ዳኞች (VAR) ተካተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰም ከአፍሪካ ከተመረጡ ሁለት የቪዲዮ ዳኞች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ ሌላኛዋ የኢሲዋቲኒ ዜግነት ያላት ቪያና ሊቺያ ሌላኛዋ የቪዲዮ ዳኝነት ግልጋሎትን የምትሰጥ ይሆናል፡፡
ፊፋ ለዚህ ውድድር ከአህጉረ አፍሪካ ሁለት ዋና እና አራት ረዳት ዳኞችንም ለውድድሩ ሲጠራቸው በህንድ በሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ላይ ጥሩ ብቃት የሚሳዩ ዳኞች በቀጣዩ ዓመት በአውስትራሊያ ለሚደረገው የሴቶች አለም ዋንጫ ላይ በቀጥታ እንደሚመርጥ ታውቋል፡፡