ሀድያ ሆሳዕና ሴኔጋላዊ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

ሀድያ ሆሳዕና ሦስተኛ የውጪ ዜጋ ተጫዋች በይፋ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡

በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ መሪነት በክለቡ መቀመጫ ከተማ ሆሳዕና የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከናወነ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና ከጋናዊዎቹ ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ስቴፈን ኒያርኮ ቀጥሎ ሶስተኛ የውጪ ዜጋ ተጫዋቹ የሆነውን ሴኔጋላዊ ግብ ጠባቂ ፓፔ ሰይዱ ኒዲያዬን በአንድ ዓመት ውል በዛሬው ዕለት የግሉ አድርጓል፡፡

1 ሜትር ከ93 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው የ29 ዓመቱ ግብ ጠባቂ አብዛኛዎቹን የእግር ኳስ ዘመኑን ለሀገሩ ክለቦች ኒያሪ ታሊ ፣ ኤ ኤስ ሲ ጃራፍ እና ጀነሬሽን ፉት በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ከዓመታት በፊትም የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አባልም ነበር፡፡

የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ወደ ዴንማርክ አምርቶ በሀገሪቱ ሦስተኛ የሊግ እርከን ተካፋይ በሆነው ጃሜርቡግት ቆይታን ያደረገ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለሀድያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፊት የአንድ ዓመት ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡