የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሚያወዳድራቸው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ፣ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ፣ የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ፣ የወንዶች አንደኛ ሊግ እና ከ 20 ዓመት በታች የሊግ ውድድሮች የዝውውር ቀናቸው ሲታወቅ በዘር እና በሀይማኖት ስያሜ የሚጠሩ ክለቦችም የስም ማሻሻያ እንዲያደርጉ ፌድሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስር የሚከናወኑ የ2015 የተለያዩ የሊግ ውድድሮች የዝውውር ቀን የሚከፈትበትን ቀን ፌድሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክቶሬት ለተሳታፊ ክለቦች በላከው መረጃ መሠረት የ2015 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ፣ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ዝውውር መፈፀም የሚችሉት ከጳጉሜ 4 – 2014 እስከ ኅዳር 15 – 2015 እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተለያያዘም ፌድሬሽኑ ከ2015 ጀምሮ በሁሉም የሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ከዘር እና ከሀይማኖት ነፃ የሆነ የክለብ መጠሪያ ስያሜን በመስጠት የከፍተኛ ሊግ መመዝገቢያ 20 ሺህ ብር ሌሎች ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ደግሞ 10 ሺህ ብር በመያዝ የተቀመጡትን መስፈርቶች በማሟላት እንዲመዘገቡም ጥሪ ተላልፏል፡፡