ነገ 10 ሰዓት የቻን የመጨረሻ ዙር የመልስ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብ ጠባቂውን ግልጋሎት እንደማያገኝ ታውቋል።
በአልጄያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ ውድድር ላይ ለመካፈል ብሔራዊ ቡድኖች በየቀጠናቸው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ዋልያውም በመጀመሪያው ዙር ደቡብ ሱዳንን ረቶ በመጨረሻው ዙር ፍልሚያ ከሩዋንዳ ጋር እንደተገናኘ ይታወቃል። ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታም ያለ ግብ አቻ ተለያይቶ የመልሱን ጨዋታ ነገ 10 ሰዓት ሩዋንዳ ሁዬ ስታዲየም ላይ ያከናውናል።
ለመልሱ ጨዋታ ታንዛኒያ ላይ ሲዘጋጅ የነበረው ቡድኑ በትናንትናው ዕለት ወደ ሩዋንዳ ያቀና ሲሆን በጨዋታው ዋዜማም የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ አከናውኗል። በዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ ደግሞ የግብ ዘቡ በረከት አማረ እንዳልተሳተፈ አውቀናል። ተጫዋቹ ታንዛኒያ በነበሩት የመጨረሻ ልምምዶች እጁ ላይ መጠነኛ ጉዳት እንዳስተናገደም ለማወቅ ችለናል። ተጫዋቹ የዛሬውን ልምምድ አለመስራቱን ተከትሎ በነገው ጨዋታ እንደማይሰለፍም ታውቋል። ከበረከት ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።