በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች አቋማቸውን ለማየት ይረዳ ዘንድ የሚደረገው የሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ በሲዳማ እና ደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን የጋራ ጥምረት እንደሚደረግ ዛሬ በተሰጠ መግለጫ ይፋ ሆኗል፡፡
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦች አቋማቸውን የሚፈትሹበት ውድድር በሀዋሳ ይካሄዳል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል መጠሪያ ይደረግ የነበረው ውድድር አሁን ላይ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ከደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ጋር በጋራ በመሆን በሀገር በቀሉ ትጥቅ አምራች ካምፓኒ ጎፈሬ ጋር በመቀናጀት ሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል መጠሪያ በሀዋሳ ከተማ ውድድሩን ለማከናወን ከሰሞኑ ሦስቱ ተቋማት የውል ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለጋዜጠኞች በሀዋሳ ሮሪ ሆቴል ስለ ውድድሩ ዓላማ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በተገናኘ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የሚደረገውን ውድድር በተመለከተ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ፣ የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ እና የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን በጋራ በመሆን መግለጫውን ሰጥተዋል፡፡
በሀገራችን በሁለት ፌድሬሽኖች የጋራ ጥምረት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከወነው ውድድር አስመልክቶ አስቀድሞ አቶ አንበሴ አበበ ከሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ባደረጉት የመግቢያ ንግግር መግለጫው ጀምሯል፡፡ “ከደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ጋር በጋራ በመሆን አምና ሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ነበር ዘንድሮ ደግሞ ሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል አንድ ላይ ለመስራት ከጎፈሬ ጋር ተስማምተን ውል ገብተናል። ይሄ ደግሞ ወደ ፊትም የሚቀጥል ነው ፤ ከሌሎች ክልሎችም ጋር ይቀጥላል። ዘንድሮ ከደቡብ ጋር አድርገናል በመቀጠል ከኦሮሚያ ጋርም ጀምረናል፡፡ ሦስት ክልሎችን ይዘን የምንቀጥል ይሆናልይሆናል። አሁን ለጊዜው ከደቡብ ክልል ጋር አውርተን በክልሉ ያሉ ክለቦች እንዲሳተፉ ተስማምተን ይሄ ውድድር ሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል ስያሜ እንዲሄድ ተስማምተን ጨርሰን ‘ውድድሩ አቋም መለኪያ ነው በደቡብ ክልል ላሉ ክለቦችም ሆነ በሲዳማ ክልል ያሉ የኦሮሚያ ክልል ክለባትም የተወሰኑ ይመጣሉ፡፡፡ ከእነርሱ ጋር ተስማምተን ጨርሰናል፡፡ ይሄ ውድድር የሚጀምርበት ቀን ደግሞ መስከረም 5 ይሆናል”፡፡ በማለት ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን የዕርስ በዕርስ ግንኙነቱን ለማጠናከርም ትልቅ መሠረት በመሆኑ ለደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ጥሪ አቅርበን በጋራ ለመስራት ፍቃደኛ መሆን መቻላቸው እንዳስደሰታቸውም ጭምር ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠል የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ “ለ2015 የውድድር ዘመን የሚዘጋጁ ክለቦችን የአቋም መለኪያ ውድድርን በጋራ ስናዘጋጅ ተነጋግረን ተወያይተን ከሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን እና ከጎፈሬ የትጥቅ አምራች ካምፓኒ ጋር የተሻለ ውድድር እናካሂዳለን ብለን እናስባለን፡፡ ይሄን ውድድር በማዘጋጀቱ ጎፈሬን እናመሰግናለን። እንደ አጠቃላይ ዓላማው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ የሁለት ክልል ክለቦችን እና ተጨማሪ ተጋባዥ ክለቦችን በመጨመር በግል ክለቦቹ ሲያካሂዱ የነበሩትን ሥልጠና ወደ ውድድር ቀይሮ ለቀጣይ የፕሪምየር ሊግ ውድድር የተሻሉ ሆነው ስህተቶቻቸውን አርመው ጎዶሎ ነገራቸውን ሞልተው ለቀጣይ ውድድር ራሳቸውን እንዲያበቁ ማስቻል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ የአቋም መለኪያ ውድድር ትልቁ ዓላማ የተጫዋቾችን አሰላለፍ አሰልጣኞች የሚያወጡበት ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውን የሚለዩበት ከመሆኑ አንፃር እንደ ክልል ብዙ ግምት ነው የምንሰጠው። ክለቦቻችን ማብቃት ነው የፌድሬሽኑ ስራ ከዚህ አንፃር ሦስታችንም ስንስማማ ትልቁ በከፍተኛ ወጪ ምንዛሬ የሚመጣውን የስፖርት ትጥቅ ካምፓኒው በቀላሉ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው ያለው። ከእርሱ ጋር መስማማት ትጥቅ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለእግርኳስ ዕድገት እና ልማት ተነሳሽነቱን የሚያሳይ በመሆኑ ይህ ቀደም ሲል ሲዳማ እግርኳስ ፌድሬሽን ብቻውን ነበር ይሄን ውድድር ሲያካሂድ የነበረው አሁን ግን ለምን በጋራ አናደርግም የሚል የተጠና ፣ የተቀደሰ ሀሳብ ይዞ በመቅረቡ እኛም እንደ ደቡብ ክልል ያሉንን ክለቦች አስተባባረን የጋራ ብናደርግ የተሻለ ይሆናል በሚል ግምት ነው አብረን ለመስራት የተስማማነው”፡፡ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል መኮንን የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ባለቤትም ንግግር አድርገዋል፡፡ “ዛሬ ይሄን መግለጫ ለመስጠት ያሰብንበት ዓላማዎች አሉት። የመጀመሪያው ዓላማ ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል ሲካሄድ የነበረውን ውድድር አሁን ዘንድሮ ደቡብ ክልልን ጨምሮ ለሌሎች አርዓያ እንዲሆን ሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል እንደምናደርግ ስም ስያሜ ቀይረናል እሱን ለማሳወቅ ነው፡፡ በሁለተኛነት አምና ከተካሄደው ተሳታፊዎችን በመጨመር ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ አዲስ ነገር ይዘን እንመጣለን ብለን አስበናል። አንዱም ይሄ ከአጎራባች ክልሎች በጋራ የመስራት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን ማሳየት ነው፡፡ በተጨማሪ አዳዲስ ክለቦችን ታዳጊዎች የሚታዩበት ከተለመደው ፎርማት ውጪ ታች ያሉትንም እንጋብዛለን፡፡” ሲሉ የትጥቅም አምራች ተቋሙ ባለቤት ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ክልል ያሉ ክለቦችን የማቀራረብ እግር ኳስ ፍቅር መሆኑን በደጋፊዎች ዘንድ እንዲኖር ማድረግ ዐላማው እንደሆነ በዕለቱ ተጠቁሟል፡፡ ውድድሩን ዳሽን ባንክ ስፖንሰር ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነ በውድድሩ ወቅት የተለያዩ አዳዲስ ሁነቶች እንደሚኖሩም ጭምር ተገልጿል፡፡