ጎፈሬ ከዩጋንዳው ክለብ ቡል ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል

👉”ከጎፈሬ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት በመፈራረማችን ደስታ ተሰምቶናል” ሚስተር ሮናልድ ባሬንት

👉”አሁን ላይ ከምስራቅ አፍሪካም አልፈን ወደ ምዕራብ አፍሪካ እየደረስን ነው” አቶ ሀሰን መሐመድ

👉”በኮንፌደሬሽን ካፕ ውድድር ላይ የጎፈሬን ጎሎ ደረታችን ላይ አድርገን በመጫወታች ደስተኞች ነን” ሚስተር ሮናልድ ባሬንት


👉”በቀጣዮቹ 5 ዓመታት በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የጎፈሬን ምርት ወስደው የሚጫወቱ ሁለት ወይም ሦስት ብሔራዊ ቡድኖችን ማግኘት እናልማለን” አቶ ሀሰን መሐመድ

ከበርካታ የሀገራችን ክለቦች ጋር በትጥቅ አቅርቦት ጉዳዮች የሚሰራው ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ምህዳሩን እያሰፋ ከሌሎች ሀገራት ክለቦች ጋር ስምምነት እየፈፀመ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህ ቀደምም ከደቡብ ሱዳኖቹ ሙኒኪ እና ማላኪያ እንዲሁም ከዩጋንዳው ሞደርን ጋዳፊ ክለብ ጋር ተፈራርሞ የመወዳደሪያ እና የመለማመጃ እንዲሁም ተያያዥ ትጥቆችን እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ አመሻሽ ደግሞ ከሌላ የዩጋንዳ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ቦሌ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ቢሮ በተከናወነው የስምምነት መርሐ-ግብር ላይ የጎፈሬ መስራች አቶ ሀሰን መሐመድ እና የቡል ክለብ ሊቀመንበር ሚስተር ሮናልድ ባሬንት ተገኝተዋል። በቅድሚያም ሁለቱ አካላት ስምምነታቸውን በፊርማ ካፀኑ በኋላ ዝርዝር ጉዳዮችን በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ማስረዳት ጀምረዋል። መድረኩን ተረክበው ንግግራቸውን ማሰማት የጀመሩት አቶ ሀሰን ተቋማቸው ተደራሽነቱን እያሰፋ ስላለበት መንገድ ሀሳብ ማጋራት ይዘዋል።

“ጎፈሬ አሁን የተፈራረመው ከአራተኛ የምስራቅ አፍሪካ ክለቡ ጋር ነው። ይሄ የሚያሳየው የጎፈሬ ትጥቅ በምስራቅ አፍሪካ ምን ያህል ተቀባይነት እያገኘ እንደሆነ ነው። በፊት ከግብፅ፣ ዱባይ እና ቻይና የሚገዙ ክለቦች ናቸው አሁን ከእኛ ጋር እየሰሩ የሚገኙት። ክለቦቹ ያለውን ጥቅም በመረዳት በዋጋም በጥራትም የተሻለ ነገር ከእኛ እየወሰዱ ነው። በዚህም ደስተኞች እንደሆኑ በሚገና እያየን ነው።

“አሁን ላይ ከምስራቅ አፍሪካም አልፈን ወደ ምዕራብ አፍሪካ እየደረስን ነው። ሳምፕሎችንም ልከን ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስምምነቶችን እየፈፀምን ነው። እኛም ግንኙነቶችን እየፈጠርን ወደ ክለቦቹ እየሄድን ነው ክለቦቹም የሌሎችን መለያ እያዩ ወደእኛ እየመጡ ነው። ክለቦቹ ወደ እኛ ሲመጡ ጥራቱን አይተው ነው። ይሄም ክለብ በፊት ከሞደርን ጋዳፊ ጋር ያደረግነውን ስምምነት አይቶ የትጥቃችንን ጥራት ተገንዝቦ ነው የመጣው። ቡል በፊት ከገበያ ነበር ትጥቅ የሚገዛው። ከገበያ የሚገዙበት ዋጋም ሆነ ጥራት ከእኛ ጋር የሚነፃፀር አይደለም። ይህንን ተከትሎ በክለቡ ወጥ ትጥቅ እንዲኖር የሚያደርግ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ነው ዛሬ እየተፈራረምን ያለነው።” ብለዋል

በማስከተል የቡል ክለብ ሊቀመንበር የሆኑት ሚስተር ሮናልድ ባሬንት የጎፈሬ ምርቶች ጥራት ጥሩ ባይሆን ኖሮ ስምምነቱን እንደማይፈፅሙ ገልፀው በስምምነቱ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በመምጣቴ በጣም ኩራት ተሰምቶኛል። መጥቼም ከጎፈሬ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት በመፈራረሜ ደስታ ተሰምቶኛል። ክለባችን ቡል በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኝ ክለብ ነው። በዚህ ዓመትም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚሳተፍ ክለብ ነው። በዚህ አህጉራዊ ውድድር ላይም የጎፈሬን ጎሎ ደረታችን ላይ አድርገን በመጫወታች ደስተኞች ነን።

“ጎፈሬ አፍሪካዊ ብራንድ ነው። እኛ ደግሞ አፍሪካዊ ብራንዶችን እንደግፋለን ፤ በተዘዋዋሪ ወንድምን እንደመርዳት ስለሆነ። በዚህም ዋነኛ ምክንያት ከጎፈሬ ጋር ለመስራት ስምምነት ፈፅመናል። ከዚህ በፊት ክለባችን ከዱባይ ነበር ትጥቅ የሚገዛው። አሁን እዚህ መጥቼ የጎፈሬን ምርቶች ሳያቸው በጣም ጥሩ ናቸው ፤ ጥራታቸውም ጥሩ ነው። ከሌሎች የውጪ ትጥቆች ጋርም መወዳደር ይችላሉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ መጥቼ ስምምነቱን በመፈራረሜ በጣም ደስተኛ ነኝ።” ካሉ በኋላ ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት እንደሚዘልቅ ጠቁመዋል። በሁለቱ ዓመታት ሦስት የመጫወቻ መለያዎችን ከጎፈሬ የሚወስደው ክለቡ በየዓመቱ 5 ሺ የደጋፊዎች መለያንም እንደሚገዛ አመላክተዋል።

ቡል በቅርቡ ላለበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የማጣሪያ ውድድር ትጥቁን መጠቀም እንደሚጀምር ሲገለፅ ይህ ዕድል ደግሞ ለጎፈሬ ትልቅ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ አቶ ሀሰን አስረድተዋል። “የጎፈሬ ህልም በጣም ትልቅ ነው። በሀገር ውስጥ ብቻ መገደብ የሚፈልግ ተቋም አይደለም ጎፈሬ። የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ምስራቅ አፍሪካ መሄዳችን አይቀርም ስንል ነበር። አሁን ህልማችን በትክክል እውን እየሆነ ነው። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የጎፈሬን ምርት ወስደው የሚጫወቱ ሁለት ወይም ሦስት ብሔራዊ ቡድኖችን ማግኘት እናልማለን። ይሄ ገና ጅማሮ ነው። በኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ የእኛ መለያ መታየቱ ሌሎች ሀገራት አፍሪካዊ ብራንድ መኖሩን የሚያዩበት ትልቅ አጋጣሚ ነው ብለን ነው የምናስበው። ከዚህ በኋላም ሌሎች ቡድኖች ይጎርፋሉ ብለን እንገምታለን።”ብለዋል።