የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ1ኛ ዙር መርሐ-ግብር ማሻሻያ ለምን ተደረገበት?

መስከረም 20 እንደሚጀመር የሚጠበቀው የቀጣይ ዓመት የሊጉ ውድድር ላይ በአንዳንድ ጨዋታዎች ማሻሻያ የተደረገበትን ምክንያት ሶከር ኢትዮጵያ አጣርታለች።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር የስፖርቱ ሚድያዎች በተገኙበት የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ዕጣ የማውጣት ፕሮግራምን ባሳለፍነው ወር ሐምሌ 26 ቀን በፅ/ቤቱ አዳራሽ ቀንና የውድድር ቦታው ሳይገልፅ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በዛን ወቅት በወጣው ፕሮግራም መሠረት በ5ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና፣ በ6ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በ14ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ ጋር እንደሚገናኙ ተገልፆ ነበር።

ሆኖም ትናንት ይፋ በተደረገው የ2015 የውድድር ዘመን የ1ኛው ዙር መርሐ-ግብር ከላይ በገለፅናቸው ጨዋታዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ታውቋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በስፖርት ቤተሰቡ ዙሪያ የመቀየሩ ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ለዚህም ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን የሊጉን አክስዮን ማኅበር ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈን አግኝተን ተከታዮን ምላሽ ሰጥተውናል።

“ የሁለት ዓመት የውድድር ዘመናችን ምን እንደሚመስል ከሱፐር ስፖርት ጋር ግምገማ አድርገናል። ብዙ ጠንካራ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ሦስት ነገሮች ላይ አተኩረት መስራት እንዳለብን ተስማምተናል አቅጣጫ ተሰጥቶበት ተለያይተናል። አንደኛው በጨዋታዎች ላይ ስታዲየም የሚገኙ ተመልካቾች ውስንነትን አይተናል። እግርኳስ ያለ ተመልካች ምንም አይነት መስብ እንደሌለው በማሰብ በርከት ያሉ ደጋፊዎች ያሏቸውን ክለቦች ውድድሩ ለሚዘጋጅበት ከተማ ቅርብ ማድረግ እንዳለብን ተስማምተናል። በዚህም መሠረት የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አስቀድሞ በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት በ5ኛ ሳምንት ባህር ዳር ላይ ቢሆንም የሚኖረው ተመልካች ውስን ነው። አዳማ ብታደርገው ግን ጨዋታው በብዙ ሺ’ዎች ተመልካች ታጅቦ የሚካሄድ በመሆኑ ለመቀየር ተገደናል።

“በተመሳሳይ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ በ6ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ብናደርገው የሚኖረው ተመልካች ጥቂት ነው። ባህር ዳር ቢሆን የሚኖረው ተመልካች መገመት ቀላል ነው። አሁን ፋሲል ከጊዮርጊስ ነው ባህር ዳር የሆነው በቀጣይ ደግሞ ሁለተኛው ዙር ሲመለስ የጊዮርጊስን ጥቅም በጠበቀ መመልኩ አዲስ አበባ ከሆነ ሊያገኘው ይችላል። ካልሆነ ግን ቅርብ በሆነው በርከት ያሉ ደጋፊዎቹን በሚያገኝበት ከተማ አዳማ ሊያገኘው ይችላል። ውድድሮች ተመልካች ሊኖራቸው ይገባል። ተመልካች ሊኖራቸው እንዲገባ ደግሞ ተመልካች ያለበት ቦታ ውድድር ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መነሻነት ከመርሐ-ግብሩ ተነስተን ብዙ ጨዋታዎችን ገለባብጠናል። የሚገርመው የሱፐር ስፖርት ገምጋሚዎች ‘ምንድን ነው ተመልካች አልባ ነው ጨዋታዎቻቹ ፤ እስካሁን ኮቪድ አለ ወይ?’ እስኪሉን ድረስ ነው አስተያየት የሰጡን። ወደ ፊት በዚህ የምንሄድ ከሆነ ስፖንሰር ማግኘት አንችልም። በመሆኑም ገብያውን መሠረት ባደረገ መልኩ ተመሳሳይ ለውጦች ይኖራሉ። ይህ አሰራር ለሊግ ካምፓኒው ሳይሆን ጥቅሙ ለክለቦች እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል። ለምሳሌ ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ አስቀድሞ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ከሆነ በ14ኛ ሳምንት አዳማ መጫወት ነበረባቸው ፤ ግን ይሄ ብዙ ተመልካች ሊኖረው የሚችል ጨዋታ በመሆኑ ወደ 3ኛ ሳምንት በማምጣት ባህር ዳር ላይ እንዲካሄድ አድርገናል።

“ሁለተኛ ያሻሻልነው የጨዋታ መጀመርያ ሰዓታችን ለተመልካች አመቺ አለመሆኑን በመረዳት ለመለወጥ መግባባት ላይ መድረስ ችለናል። ለምሳሌ የአራት ሰዓት ጨዋታ ከዚህ በኋላ የሚቀር ይሆናል። ይህ ሰዓት ሊጉ እንደ መጀመርያ መሆኑ መጠን ሊቀበሉን ይችላሉ። ከዚህ በኋላ ግን ተመልካች የሚስብ ብዙ ተመልካች ያለው ውድድር መሆን እንዳለበት በማመን ሜዳቸው መብራት የሌላቸው ከተሞች ጨዋታዎቹ ሰባት እና አስር ሰዓት እንዲሆኑ እና መብራት ያላቸው ሜዳዎች ደግሞ ዘጠኝ እና አስራ ሁለት ሰዓት እንዲሆኑ ተደርጓል።

“ሦስተኛው ማሻሻያ የተደረገው ውድድሩን የሚያዘጋጁ ከተሞች ከዚህ ቀደም የመክፈቻ ጨዋታዎችን አያደርጉም ነበር። አሁን ባደረግነው ለውጥ ሦስቱም ከተሞች ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና አዳማ የመክፈቻ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ ተደርጓል። ይህ ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረግነው ውይይት ያደረግነው መልካም ለውጥ ነው።” በማለት በመርሐ-ግብር ለውጦቹ ላይ የተደረጉትን ለውጦች ካብራሩልን በኋላ የማጠቃለያ ንግግራቸውን አጋርተውናል።

“በአጠቃላይ አወዳዳሪው አካል ዘንድሮ በጠንካራ ሁኔታ ወደ ገብያ የሚገባበት ጊዜ ነው። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የቅስቀሳ ስራዎችን በተለያዮ መንገዶች እንሰራለን። የሊጉን ጥራት እና ዕድገት ለመጠበቅ መጠነ ሰፊ ስራ ይሰራል። በዚህ ስራ ውስጥ አንዱን ክለብ ለመጥቀም ሌላውን ለመጉዳት የሚሰራ ስራ አለመኖሩን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ሊጋችን ስፖንሰሮችን የሚስብ፣ ዐይን ውስጥ እንዲገባ እና በብዙ ደጋፊዎች ታጅቦ የሚካሄድ እንዲሆን እንፈልጋለን። አስቀድመን ክለቦችን ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ስልጠና አስተምረናል። ‘እባካቹሁ ደጋፊዎችን በመሳብ አምጡ፣ ስፖንሰር ፍለጋ ላይ ከፍተኛ ስራ ስሩ’ ብለናል። ሊጉን የእነርሱ ነው ፤ ሊጠብቁት እንደሚገባም ማብራሪያ ሰጥተናቸዋል።” በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።