የ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኞች ታውቀዋል

በሞሮኮ አዘጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኞቹ ታውቀዋል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት የ2023 የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር በሞሮኮ አስተናጋጅነት ራባት ከተማ ላይ ይደረጋል፡፡ በዚህም ውድድር ላይ ሀገራት ተካፋይ ለመሆን በቅድመ ማጣሪያ ውድድር አስቀድመው የሚሳተፉ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም በቀጣዩ መስከረም ወር ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር የማጣሪያ ጨዋታዋን ታከናውናለች፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከሳምንታት በፊት አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙን በዋና አሰልጣኝነት በብሔራዊ ቡድኑ በመቅጠር ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ቡጣቃ ሻመናን ከአርባምንጭ ከተማ 36ኛ ተጫዋች በማድረግ በአሰልጣኙ መሪነት በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፊያቸውን አድርገው ዝግጅት መስራት ጀምረዋል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችሁ መረጃ መሠረት ከሆነ የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ሁለት ረዳቶት ታውቀዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ውስጥ ያለፉት ረዘም ያሉ ዓመታት በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ሀብታሙ ዳዲ የብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ሲሾም ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ እንዲሁም በአሰልጣኝነት በሰበታ ከተማ እንዲሁም ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ጀምሮ ደግሞ የቀድሞ ክለቡን ሀዋሳ ከተማ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት እያገለገለ የሚገኘው አዳሙ ኑሞሮ የብሔራዊ ቡድኑ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ተመርጧል፡፡