በክለቡ መቀመጫ ከተማ በሆነችው ሆሳዕና የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና የአንድ ተጫዋች ዝውውር ሲፈፅም የተከላካዩንም ውል አራዝሟል፡፡
ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የተጫዋች ዝውውር ላይ በንቃት ተሳትፎን ያደረገው ሀድያ ሆሳዕና በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በክለቡ መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ እየከወነ የሚገኝ ሲሆን አንድ ተጨማሪ ተጫዋች ማስፈረሙም ታውቋል።
መለሰ ሚሻሞ የክለቡ አዲሱ ተጫዋች ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተሳታፊ በሆነው ሀድያ ሌሞ እና የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ቡራዩ ከተማ ያሳለፈው አማካዩ የተሰጠውን የሙከራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀሙ በሁለት ዓመት የውል ዕድሜ አዲሱ የክለቡ ተጫዋች ሆኗል፡፡
ሀዲያ ከአዲስ ፈራሚው በተጨማሪ ከክለቡ ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሊጉ ጥሩ አቋሙን ሲያሳይ የነበረውን ወጣቱ ተከላካይ ቃልአብ ውብሸትን ቆይታም ለሁለት ተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።