አዳማ ከተማ ሁለት የጋና ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች አስፈረመ

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ መሪነት በባቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኘው አዳማ ከተማ ሁለት ጋናዊ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል፡፡

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በዋና የአሰልጣኝነት መንበር ከሾመ በኋላ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም ከቀናት በፊት በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን መከወን የጀመረው አዳማ ከተማ የጋና ዜግነት ያላቸውን ግብ ጠባቂ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን በአንድ ዓመት ውል በይፋ አስፈርሟል፡፡

1 ሜትር ከ 86 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ግብ ጠባቂው ኮዋሜ ባህ አዲሱ የአዳማ ጋናዊ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ለሀገሩ ክለቦች ኸርትስ ኦፍ ላይን ፣ ኢንተር አሊስ እና አሳንቲ ኮቶኮ ተጫውቶ ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ቀጣይ መዳረሻው የኢትዮጵያው ክለብ አዳማ ሆኗል፡፡

ሌላኛው ጋናዊ የአጥቂ አማካይ ተጫዋቹ ፍሬድሪክ አንሳህ ቦችዌ አዳማን በይፋ ተቀላቅሏል፡፡ በሀገሩ ክለቦች ሌበርቲ ፕሮፌሽናል እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ ተጫውቶ ያሳለፈው የ25 ዓመቱ አማካይ አዳማ ከተማን በይፋ መቀላቀሉ ዕውን ሆኗል፡፡

ያጋሩ