በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ክለቦች በድጋሚ የወዳጅነት ጨዋታ ነገ ያከናውናሉ፡፡
በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተካፋይ የሆነው የሱዳኑ ክለብ አል-ሜሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በድጋሚ የወዳጅነት ጨዋታን እንደሚያደርግ በይፋዊ የማኅበራዊ ገፁ ጠቁሟል፡፡ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያዊያኑ ዳኞች ቴዎድሮስ ምትኩ ፣ ተመስገን ሳሙኤል ፣ ፋሲካ የኋላሸት እና አሸብር ሰቦቃ መሪነት ከአርታ ሶላር ጋር ጨዋታ ያለው ክለቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የመልስ ጨዋታውንም እዚሁ ሀገራችን ላይ ለማድረግ መወሰኑን በተለያዩ ዘገባዎቻችን ገልፀን ነበር፡፡
ከቀናት በፊት የሀገራችን ክለብ ከሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታን ያደረገው ክለቡ ሦስተኛ የወዳጅነት ጨወታውን በነገ ዕለት እንደሚያደርግ አሳውቋል፡፡ በዚህም በቻምፒየንስ ሊጉ ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር የሚጫወተው እና ከቀናት በፊት አል-ሜሪክን አሸንፎ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ልምምዱን በሚያደርግበት ቢሾፍቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ነገ ማክሰኞ ሜሪክን ይገጥማል።