በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ወደ ሁለተኛው ሊግ የወረደው ሰበታ ከተማ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እንዳይሳተፍ እግድ ተላልፎበታል።
ያለፉትን ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው ሰበታ ከተማ በተጠናቀቀው ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይታወቃል። የውድድር ዓመቱን ከተጫዋቾች የደሞዝ እና ጥቅማጥቅም እንዲሁም ከአሠልጣኞች መግባት እና መውጣት ጋር ተያይዞ ስሙ ሲነሳ የነበረው ክለቡም በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ የነበሩበት ምስቅልቅሎች ተፅዕኖ ፈጥረውበት እንደነበር አይዘነጋም። በተለይ የክለቡ ተጫዋቾች ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም አልተሰጠንም በማለት ልምምድ እስካለመስራት ደርሰው የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም ጉዳዩን ተመልክቶ በቀነ ገደብ ተጫዋቾቹ ወደ ውድድር እንዲመለሱና ክለቡ የሚጠበቅበትን ገንዘብ ለተጫዋቾቹ እንዲፈፅም ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ይህ ቢሆንም ግን የክለቡ ተጫዋቾች የነበሩት አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ በኃይሉ ግርማ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ለዓለም ብርሃኑ፣ ፍፁም ገብረማርያም፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ ገዛኸኝ ባልጉዳ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ምንተስኖት አሎ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ አለመደረጉን ባስገቡት የአቤቱታ ደብዳቤ ክለቡ ውሳኔውን ተግባራዊ ባለማድረጉ ከተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እንዲታገድ መወሰኑን ጉዳዩን የያዙት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።