የጣና ካፕ የሚጀመርበት ቀን ታውቋል

የሀገር ውስጥ እና ሁለት የውጪ ክለቦችን በማሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ የሚከናወነው የጣና ካፕ የስያሜ መብት በማግኘት በደማቅ ሁኔታ ይደረጋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ በጋራ በመሆን የጣና ካፕ ውድድርን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩ ይታወቃል። ለመጀመሪያ ጊዜ በውቢቷ ባህር ዳር ከተማ እንደሚዘጋጅ የሚጠበቀው ውድድርም የቀጣይ ዓመት የሊጉ ፍልሚያ ከመጀመሩ በፊት እንዲደረግ የቅድመ ስራዎች ሲከወኑ ቆይተው አብዛኞቹ ተግባራት እንደተጠናቀቁ የውድድሩ የማኅበራዊ ሚዲያ አጋር የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ ከአዘጋጆቹ ለማወቅ ችላለች።

ውድድሩም በአራት የሀገር ውስጥ እና ሁለት የውጪ ክለቦች መካከል ከመስከረም 6 ጀምሮ እንደሚከናወን ታውቋል። የሊጉ ውድድር በባህር ዳር ከተማ መጀመሩን በመንተራስ እንዲሁም በባህር ዳር ያለውን የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የውድድር ሜዳዎች እና ማረፊያዎች ጥራት ታሳቢ በማድረግ በርካታ ክለቦች በዚህ ውድድር ላይ ለመካፈል ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸው ሲታወቅ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ውድድሩን በውስን ክለቦች መካከል ብቻ ለማድረግ መወሰኑን ታውቋል። ክለቦችን የመለየት ሥራም እየተጠናቀቀ እንደሆነ ተመላክቷል።

ከሀገራችን ክለቦች ውጪ ጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ከእህት ኩባንያው ጎፈሬ ስፖርት ኢቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በመሆን በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ሁለት ክለቦችን ለማምጣት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ተገልጿል።

በተያያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወነውን ውድድር በደማቅ ሁኔታ ለማከናወን አጋር ተቋማት እየተፈለጉ የሚገኝ ሲሆን የውድድሩ የሥያሜ መብት ገዢም ተገኝቷል።