ከመስከረም 6 ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ የሚደረገው ውድድር የስያሜ መብት ስፖንሰር ሲያገኝ ከነገ በስትያ በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫም ስምምነቱ ይፋ እንደሚሆን ታውቋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ የሚከናወነው የጣና ካፕ ውድድር በስድስት ክለቦች መካከል ከመስከረም 6 ጀምሮ እንደሚከናወን ከሰዓታት በፊት ዘገባ ማቅረባችን ይታወቃል። በዘገባችን ላይም ውድድሩን በደማቅ ሁኔታ ለማከናወን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝና የሥያሜ መብቱንም ለመሸጥ እየተንቀሳቀሱ እንደነበር አመላክተን ነበር። ይሁ ውጥን ተሳክቶ የሥያሜ መብቱን አማራ ባንክ እንደወሰደው የውድድሩ የማኅበራዊ ሚዲያ አጋር ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ይህንን ስምምነት አስመልክቶም ከነገ በስትያ ሀሙስ 3 ሰዓት ለገሀር በሚገኘው የአማራ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን አዲሱ የውድድሩ ሎጎ እና ሥያሜም ይፋ እንደሚሆን ተመላክቷል።