የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሜዳ ላይ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ታውቋል

የ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያለበትን የሜዳ ላይ ጨዋታ የሚያደርግበት ስታዲየም ተለይቷል።

በአሠልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላሉበት ጨዋታዎች ዝግጅቱን በካፍ የልህቀት ማዕከል እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በመጀመሪያው ዙር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻውን የሚገጥመው ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን በሜዳው እንዲያደርግ በእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱ መርሐ-ግብር ተይዞ የነበረ ሲሆን በሀገራችን በካፍ ፍቃድ ያገኘ ሜዳ አለመኖሩን ተከትሎ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ጉዳይ ሲጠበቅ ቆይቷል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት ግን ብሔራዊ ቡድኑ የሜዳ ላይ ጨዋታውን በመዲናችን አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲያደርግ ፍቃድ አግኝቷል። በዚህም የመጀመሪያ ጨዋታውን መስከረም 12 በደጋፊው ፊት ሲያከናውን የመልስ ጨዋታውን ደግሞ መስከረም 17 ኮንጎ ላይ የሚከውን ይሆናል።