ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር ተከናወነ

በመዲናችን አዲስ አበባ በሚከናወነው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ለሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን የአሠልጣኝ ቅጥር መከናወኑ ይፋ ሆነ።

በአልጄርያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ሀገራት የቀጠናቸው ተከፋፍለው የማጣርያ ውድድር የሚያከናውኑ ሲሆን የዚህ አካል የሆነው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከመስከረም 20 ጀምሮ ይከናወናል። በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ለማዘጋጀትም ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች መሾሙን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው አሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ነው። ወጣቱ አሰልጣኝ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሴቶች ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን የሰራ ሲሆን ዘንድሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 ዓመት በታች ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ከቡድኑ ጋር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታት ውድድር ሻምፒዮን መሆን ችሎ ነበር።

በምክትል አሰልጣኝነት ደግሞ ራሕመቶ መሐመድ እና ዐቢይ ካሣሁን ተሹመዋል። አሰልጣኝ ራሐመቶ ከዚህ ቀደም በባቱ ከተማ ፣ ነገሌ አርሲ እና ሞጆ ከተማ በዋና አሰልጣኝነት የሰራ ሲሆን ዘንድሮ በድጋሚ ነገሌ አርሲን በማሰልጠን በከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በተጨማሪም ከ17 ዓመት በታች የክልሎች ሻምፒዮና የኦሮሚያ ምርጥን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ከቡድኑ ጋር ሻምፒዮን ሆኗል። አሰልጣኝ ዐቢይ በበኩሉ ከዚህ ቀደም በፓሽን ስፖርት አካዳሚ ፣ አሴጋ ስፖርት አካዳሚ እና ሀሌታ ስፖርት አካዳሚ የሰራ ሲሆን ዘንድሮ በተካሄደው ከ17 ዓመት የክልሎች ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ምርጥን በማሰልጠን ከቡድኑ ጋር ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም።