የፈረሰኞቹ አጥቂ ከእሁዱ ጨዋታ ውጭ ሆኗል

በዘመን መለወጫ ዕለት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያውን ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ የሚያደርጉት ፈረሰኞቹ በወሳኙ ፍልሚያ የአጥቂያቸውን ግልጋሎት አያገኙም።

ሀገራችንን በመወከል መስከረም አንድ በባህር ዳር ስታዲየም የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያውን ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከሱዳኑ አል ሂላል ኦምዱርማን ጋር የሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዝግጅታቸውን ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በቢሸፍቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ሲሰሩ ቆይተዋል።

ለወሳኙ ፍልሚያ እንዲረዳቸው ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታቸውን ከታንዛኒያው ሲምባ እና ከሱዳኑ ኤል ሜሪክ ጋር ማድረጋቸውም ይታወሳል። የፊታችን እሁድ በዘመን መለዋጫ ዕለት የመጀመርያ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከሱዳኑ አል ሂላል ኦምዱርማን ጋር የሚያደርጉት ፈረሰኞቹ የአጥቂያቸውን አቤል ያለውን ግልጋሎት እንደማያገኙ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። ተጫዋቹ ያለፉትን ሦስት ሳምንታት ባጋጠመው ጉዳት ከልምምድ የራቀ ሲሆን ይህን ተከትሎ ለእሁዱ ጨዋታ እንደማይደርስ ተረጋግጧል።

የቡድኑ አባላት ለእሁዱ ጨዋታ ነገ ከሰዓት ባህር ዳር ከተማ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።