የአማራ ባንክ የጣና ዋንጫን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

በአምስት ሚሊዮን ብር የአማራ ባንክ የጣና ዋንጫ በሚል መጠሪያ የሚደረገውን ውድድር የሥያሜ መብት ባለቤትነት በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ እና በጎፈሬ አዘጋጅነት የሚከናወነው የጣና ዋንጫ ውድድር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ሁለት የውጪ ክለቦችን በማሳተፍ እንደሚደረግ ይታወቃል። ውድድሩን ደማቅ ለማድረግ ሁለቱ አካላት ስራዎችን ሲሰሩ የሰነበቱ ሲሆን የውድድሩን የሥያሜ መብት ለመሸጥም እንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩ ከሰሞኑን ዘገባ አቅርበን ነበር። ይሁ ውጥን ዕውን ሆኖ አማራ ባንክ የውድድሩ የሥያሜ መብት ባለቤት መሆኑ ይፋ ሆኗል።

ስምምነቱን አስመልክቶ ዛሬ በአማራ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም፣ የአማራ ባንክ ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ዳይሬክተር
አቶ አስቻለው እንዲሁም የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ባለቤት አቶ ሳሙኤል ተገኝተዋል። በቅድሚያ አቶ አብርሃም እና አቶ አስቻለው ስለ ስምምነቱ ገለፃ ከመደረጉ በፊት የፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውነዋል። በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ፊት ስምምነቱ በይፋዊ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ከፀና በኋላም ዝርዝር ገለፃዎች መደረግ ይዘዋል።

ከመስከረም 6 እስከ 14 ድረስ እንደሚደረግ ይፋ የሆነው የአማራ ባንክ የጣና ዋንጫ ውድድር በሀገራችን ከፍተኛ የሊግ ዕርከን የሚሳተፉ ክለቦችን ከተጋባዥ የውጪ ክለቦች ጋር በመቀላቀል የሚደረግ ሲሆን ተሳታፊ ክለቦችም በውድድሩ ለመሳተፍ ይሁንታቸውን እየላኩ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የሥያሜ መብቱን የወሰደው እና “ከባንክ ባሻገር” በሚል መሪ ቃል በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው አማራ ባንክ ማኅበረሰቡን የዋጀ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አስቻለው ባንኩ የሥያሜ መብቱን የገዛበትን ምክንያት እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል። “ስፖርት ማኅረበሰብን ያቀራርባል። ይህ የእግርኳስ ውድድር በመደረጉ ከታችኛው የስራ መደብ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ያለው የከተማው ኢኮኖሚ ይነቃቃል። ይህ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ይህንን ለማድረግ ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ ጋር በጋራ ለመስራት በመቻላችን ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል።” ብለዋል።

አቶ አብርሃም በበኩላቸው በሀገር እና በክልሉ ተዳክሞ የነበረውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በስፖርታዊ ውድድሮች ለማነቃቃት እየተሰራ እንደሆነ ያመላከቱ ሲሆን አሁንም የቅድመ ውድድር ዝግጅት አካል እንደሆነ የሚታሰበውን ውድድር ከዋናው የሊግ ጅማሮ በፊት ለማድረግ በመቻሉ ከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ደስታ እንደሚሰማው በንግግራቸው ገልፀዋል።

መድረኩን በማስከተል የተረከቡት አቶ ሳሙኤል ጎፈሬ የስፖርት ኩነቶችን የማሰናዳት ያለውን ልምድ በመጠቀም ውድድሩን ለማድመቅ እንደሚንቀሳቀስ ገልፀው ከሊጉ ክለቦች ውጪ በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉት ሞደርን ጋዳፊ እና ቡል ኤፍ ሲ ለማሳተፍ ስራዎች እንደተገባደዱ ይፋ አድርገዋል። ጨምረውም በውድድሩ አዳዲስ ነገሮች እንዲኖሩት እንደሚደረግ ጠቁመው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

የውድድሩ የሥያሜ መብት በ5 ሚሊዮን ብር መሸጡ በመግለጫው የተነገረ ሲሆን በውድድሩም ከ6 እስከ 8 ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሏል። የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ጅማሮ በባህር ዳር ከተማ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ክለቦች የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፋቸውን በከተማው ለማድረግ ማሰባቸው ለውድድሩ ድምቀት እንደሚፈጥር ከመድረኩ ሲንፀባረቅ ክለቦች በውድድሩ የሚያገኙትን ሽልማት በተመለከተ ግን በሚስጥር ተይዞ ወደፊት ይፋ እንደሚሆን ተገልጿል።