በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሀገራችን ተወካይ ፋሲል ከነማ እና የቡሩንዲው ክለብ ቡማሙሩ የሚያደርጉት ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚያገኝ ታውቋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ በአህጉራችን ሁለተኛ የክለቦች ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕድል ያገኘ ሲሆን የማጣሪያ ጨዋታዎችንም ከዛሬ ጀምሮ ማከናወን ይጀምራል። ዛሬ 10 ሰዓትም በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር የቡሩንዲውን ቡማሙሩ በባህር ዳር ስታዲየም የሚያስተናግድ ይሆናል። ይህንን ጨዋታ ስታዲየም ተገኝተው መመልከት የማይችሉ ደጋፊዎችም በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲመለከቱ ክለቡ ጥረት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ይህ ውጥንም ተሳክቶ ጨዋታው በቴሌቪዥን እንደሚታይ አውቀናል።
በዚህም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቴሌቪዥን አማራጩ (አማራ ቲቪ) ጨዋታውን ከ10 ጀምሮ ለማስተላለፍ የካሜራ ገጠማን ጨምሮ የቴክኒክ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል። አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስም ጨዋታው ለተመልካች እንደሚደርስ ተጠቁሟል።