ዐፄዎቹ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ፋሲል ከነማ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቡሩንዲውን ቡማሙሩ ገጥሞ 3ለ0 በማሸነፍ የማጣሪያ መርሐ-ግብሩን በድል ጀምሯል፡፡

የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በተለያዩ የአህጉራችን ሀገራት ዛሬ መደረግ ሲጀምር በውድድሩ ሀገራችንን የሚወክለው ፋሲል ከነማም 10 ሰዓት ላይ የብሩንዲውን ቡማሙሩ ገጥሟል፡፡ ፋሲል ከነማዎች በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ አዲሱን የክለቡ ፈራሚ ሀብታሙ ገዛኸኝን በቋሚ አሰላለፍ በማካተት ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዳው ክለብ ቡማሙሩ በበኩሉ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ቀርቧል፡፡ ዐፄዎቹ ብልጫ ወስደው መጫወት በቻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሜዳውን በአግባቡ በመለጠጥ ወደ መስመር አድልተው መጫወት የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ቡማሙሩዎች ጥንቃቄ አዘል ነገር ግን በፈጣን የጨዋታ ሽግግር ለመጫወት የጣሩበትን ሂደት ማስተዋል ችለናል፡፡

በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው በአጋማሹ ብልጫን ማሳየት የቻሉት ዐፄዎቹ በሀብታሙ ገዛኸኝ የ6ኛ ደቂቃ ሙከራ ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ማድረግን ጀምረዋል፡፡ የጨዋታው ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዩ መሀል ሜዳ ላይ በሚፈጥሩት ድንቅ መግባቦት በመስመር በኩል በሁለቱም ኮሪደሮች ወደ ተሰለፉት ሀብታሙ እና አለምብርሀን በማሻገር ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተደጋጋሚ የቡማሙሩን የግብ ክልል በበዛብህ ፣ ሀብታሙ እና ሽመክት አማካኝነት በተደጋጋሚ ለመፈተሽ ጥረት ያደረጉት ፋሲሎች 17ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ ላይ በሳጥኑ ጠርዝ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል አክርሮ ሲመታ ግብ ጠባቂው ፓተንት እንደምንም ይዞታል፡፡

32ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ በምክትል አሰልጣኙ ምንተስኖት ጌጡ እየተመሩ የነበሩት ፋሲሎች ግብ አግኝተዋል፡፡ ከማዕዘን ምት ሱራፌል ዳኛቸው ሲያሻማ ወጣቱ የመስመር ተጫዋች አለምብርሀን ይግዛው ከተከላካዮች መሀል አፍትልኮ ወጥቶ በግንባር በመግጨት ከመረብ ያሳረፋት ግብ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ጥንቃቄን የመረጡ ይመስሉ የነበሩት ቡማሙሩዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ አጥቂው ሻሂርና አማና ከርቀት አክርሮ ሲመታ ለጥቂት ኢላማዋን ስታ የወጣችባቸው ዕድል ብቸኛዋ የቡድኑ ሙከራ ሆናለች፡፡

በሱዳናዊው የመሀል ዳኛ አብደላ ኢሳላንጎ መሪነት ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ፋሲሎዎች ሀብታሙ ገዛኸኝን አስወጥተው በምትኩ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ሜዳ ለውጠው አስገብተዋል፡፡ ቡማሙሩዎች ደግሞ ከመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ አሰላለፍ ወደ 4-4-2 በመቀየር የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስተካከል ሙከራን አድርገዋል፡፡ መሀል ክፍል ላይ ተመጣጣኝነት ያለውን እንቅስቃሴ ሁለቱም ክለቦች ማሳየት ቢችሉም በይበልጥ ለጎል የቀረቡ ይመስሉ የነበሩት ዐፄዎቹ ነበሩ፡፡ ለዚህም ማሳያው በአንድ ሁለት ቅብብል የሚፈጥሯቸው ዕድሎች ማሳያ ናቸው፡፡ 63ኛው ደቂቃም ሁለተኛ ጎላቸውን ፋሲሎች ከመረብ አዋህደዋል፡፡ ማሊያዊው ግብ ጠባቂ ሳማኪ ከግብ ክልሉ በረጅሙ የላከውን ኳስ አጥቂው ፍቃዱ አለሙ የቡማሙሩ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድኑን ወደ 2ለ0 አሸጋግሯል፡፡

ቡማሙሩች በጨዋታ እንቅስቃሴ ጥሩ የነበሩ ቢመስሉም የፋሲሎች የበላይነት ግን የሚቻል አልሆነም። 78ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ከድር ኩሊባሊ አግኝቶ ወደ ግብ ሲመታው ግብ ጠባቂው ፓተንት አውጥቷል፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ፋሲል ከነማዎች የግብ መጠናቸውን ያሰፉበትን ጎብ አግኝተዋል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘን ዕድል ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ዐፄዎቹን በክረምቱ የተቀላቀለው ታፈሰ ሰለሞን ሁለት ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂን ጭምር በማለፍ ሦስተኛ ጎል በአስገራሚ አጨራረስ ለክለቡ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ቡማሙሩዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ 83ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ኡማር ንጋላንዴ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ሚካኤል ሳማኪ እንደምንም አድኖበታል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎችን ሳንመለከት በፋሲል ከነማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የመልሱ ጨዋታ ከቀናት በኋላ በገለልተኛ ሜዳ ታንዛኒያ አዛም ኮምፕሌክስ የሚደረግ ይሆናል።

ያጋሩ