የዐፄዎቹ ዋና አሰልጣኝ ካስመዘገቡት ድል በኋላ በጨዋታው ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
ፋሲል ከነማ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የብሩንዲው ቡሙማሩን ባህር ዳር ላይ 3-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተዋል።
ስለጨዋታው...
“ጨዋታውን የጠበኩት ነው የነበረው። ምናልባት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ተደጋጋሚ አለማድረጋችን ትንሽ የመፍዘዝ ነገሮች ነበሩ። ነገር ግን ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ስናገኝ የተሻለ ቡድን እንሰራለን። ከሞላ ጎደል ግን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል።
ስለተጋጣሚ…
“አዎ ጠብቀን ነበር። ከሜዳህ ውጪ ስትጫወት ጥንቃቄ አድርገህ ነው የምትጫወት ፤ ወርደው እንደሚጫወቱ አውቀን ነበር። ‘ያንን ደግሞ በምን መልኩ ነው ማስቆጠር ያለብን ?’ እሱን ነገር ነው ተነጋግረን የነበረው። የምንፈልገውን ነገር ልጆቹ አድርገዋል ፤ ያውም የወዳጅነት ጨዋታ ሳናደርግ። ይህ ጥሩ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው።
ስለቡድኑ አቅም…
“ቡድኔ ከዚህ በፊትም ተናግሬዋለሁ በተደጋጋሚ ከዚህ በላይ መሄድ የሚችል አቅም ያለው ቡድን ነው። የተጫወቱት ብቻ ሳይሆን ውጪም ያሉት የተሻለ አቅም ያለቸው ተጫዋቾች አሉ። ያልተጫወቱት ከቡድኑ ጋር እስኪላመዱ ነው ሲዋሀዱ የተሻለ ነገር የሚሰራ ቲም ይኖረናል ብየ አስባለሁ ዘንድሮ።
ስለመልሱ ጨዋታ…
“ከሜዳችን ውጪ ሁለታችንም ከሜዳ ውጪ ነው የምንጫወተው ፤ ዕኩል ዕድል ነው ያለን። ምንአልባት እነሱ ዕድል ሊወስዱ የሚችሉት ሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ መጫወታችን ነው። እኛም የተወሰኑ ልምምዶችን እዛ ሜዳ ላይ ለመሥራት አስበናል። እናም ጥሩ ውጤት ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።
ስለ ውድድሩ ዕቅዳቸው…
“እኛ እንግዲህ ከዚህ በፊት የመጀመሪያው ዙር ላይ ነው የምንወጣው። ስለዚህ ከዚህ የተሻለ ለመሄድ ነው ሀሳባችን ያንን ደግሞ እናሳካዋለን ብለን ነው የማምነው።”