የቡሙማሩ ዋና አሰልጣኝ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ኃሳባቸውን አጋርተዋል።
በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ያስተናገደው የቡሙማሩ ቡድን አሰልጣኝ ቪቪየር ባሃቲ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
ስለጨዋታው…
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ፋሲሎች ጨዋታውን በማፍጠን ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። የመጀመሪያውን ጨዋታ ተሸንፈናል። ነገር ግን በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ነገር ለማስመዝገብ እንዘጋጃለን።
ስለመልሱ ጨዋታ…
“ተስፋ እናደርጋለን በመልሱ ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ እናደርጋለን ብለን እናስባለን ፤ በመልሱ ጨዋታ ተለውጠን መቅረብ ይኖርብናል። ተለውጠን ከቀረብን የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን።
ስለፋሲል ከነማ…
“ፋሲሎችን ከዚህ ቀደም አውቃቸው ነበር። በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ አዎንታዊ ለውጦችን አድርገዋል። ይህም የቡድኑን ደረጃ ከፍ አድርጎታል። ከአዛም ጋር መጥቼ ከተመለከትኩት በጣም ተሻሽለው የባለፈው ሦስት ዓመት ሥራቸው ለዛሬው ውጤት አብቅቷቸዋል ብዬ አስባለሁ።
ስለፋሲል ደጋፊዎች…
“ደጋፊዎቹ ጥሩ ናቸው ፤ እንደተመለከታችሁት ስታዲየሙ በደጋፊ ተሞልቶ ነበር። ይህም ተጫዋቾቻቸውን በማነሳሳት እና ጥሩ እንዲጫወቱ በማድረጉ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበረው።
ስለመጫወቻ ሳሩ…
“ተፈጥሮአዊ ሳር መሆኑ ደስ ይላል ፤ ሜዳውም የተያዘበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው።”