ከነገው ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ በፈረሰኞቹ ቤት ያሉ ወቅታዊ መረጃዎችን እናጋራቹሁ

ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ቻምፒየንስ ሊግ መድረክ የተመለሱትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተመለከቱ አሁናዊ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ሀገራችንን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ለመወከል ከነገ ጀምሮ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል። የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል ባወጣው መርሐ ግብር መሰረትም ከሱዳኑ ኃያል ክለብ አል-ሂላል ኦምዱርማን ጋር በቅድመ ማጣሪያው ተደልድለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሐምሌ 16 ጀምሮ መቀመጫቸውን በቢሸፍቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ በማድረግ ሲዘጋጁ የቆዩ ሲሆን ወቅታዊ አቋማቸውን የሚያዩበት ሁለት ጨዋታዎችን ከታንዛኒያው ሲምባ እና ከሱዳኑ ኤል-ሜሪክ ጋር ማድረጋቸው አይዘናም። በዝግጅታቸው ግን በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በወጥነት የዝግጅታቸው አካል አለማድረጋቸው እንደ ክፍተት ሲነሳባቸው ቆይቷል።

ነገ በአዲሱ ዓመት አዲስ ቀን አስር ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም ወሳኝ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት ፈረሰኞቹ የአቤል ያለውን ግልጋሎት እንደማያገኙ አስቀድመን ያጋራናችሁ ሲሆን ተጫዋቹም በዚህ ጨዋታ ከቡድኑ ስብስብ ውጪ በመሆን ወደ በባህር ዳር እንዳልተጓዘ አውቀናል። ሌላው እስካሁን ማረፊያው ያልታወቀው አማኑኤል ገብረሚካኤል ባሳለፍነው ሐሙስ ፈረሰኞቹ ከኤል-ሜሪክ ጋር ያደረጉትን ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ወደ ቢሸፍቱ በመጓዝ የተከታተለ ቢሆንም በነገው ጨዋታ ከቡድኑ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።

ዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት ጨዋታውን በሚያከናውኑበት ሜዳ ለአንድ ሰዓት በቆየው ልምምዳቸው ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን እና በነገውን ጨዋታ ቋሚ አስራ አንድ ሊሆኑ የሚችሉትን ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍለው በጥሩ የቡድን መንፈስ ሲለማመዱ ተመልክተናል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ አል-ሂላል ኦምዱርማን በርከት ያሉ የቡድኑን አባላት በመያዝ ሐሙስ አመሻሽ ባህር ዳር የገባ ሲሆን ማረፊያውን በዮኒሰን ሆቴል በማድረግ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

ጨዋታውን በዋናነት የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከጅቡቲ ሲሆኑ አስቀድሞ የጨዋታው ኮሚሽነር በመሆን ተመድበው የነበሩት ኤርትራዊው ባለሙያ በተለያዮ ምክንያቶች እንደሌሉ እና የትናቱን ፋሲል ከነማን ከቡማሙሩ ያደረጉትን ጨዋታ በኮሚሽነርነት የመሩት ዮጋንዳዊው ባለሙያ በድጋሚ ይህን ጨዋታ እንዲታዘቡ መመደባቸውን አውቀናል። ነገ አስር ሰዓት በሚካሄደው በዚህ ወሳኝ ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ዋጋ 30፣ 50፣ 100 እና 500 ብር መሆኑን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ ገልፀውልናል።

ፈረሰኞቹ ይህን ጨዋታ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት ድል የሚያደርጉ ከሆነ የታንዛንያው ያንግ አፍሪካ እና የደቡብ ሱዳኑ ዛላን አሸናፊን የሚፋለሙ ይሆናል።

ያጋሩ