አል-ሂላል ኦምዱርማን የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

ከቀናት በፊት ባህር ዳር የደረሰው አል-ሂላል ኦምዱርማን በባህር ዳር ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቶ አጠናቋል።

ነገ አስር ሰዓት በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገው የሱዳኑ ክለብ አል-ሂላል ኦምዱርማን ሐሙስ ባህር ዳር መድረሱን ይታወሳል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 1930 የተመሰረተው ይህ አንጋፋ ቡድን 23 ተጫዋቾችን እና አሰልጣኞቹ አባላትን ጨምሮ በአጠቃልይ ከአርባ በላይ ልዑክ በመያዝ ወደ ሀገራችን የመጣ ሲሆን ማረፊያውንም በዮኒሰን ሆቴል አድርጎ የጨዋታውን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል።

ከካሜሮን፣ ከአንጎላ ፣ ከናይጄሪያ፣ ከሴኔጋል፣ ከአይቬሪኮስ (ሁለት)፣ ከዲሞክራቲክ ኮንኮ፣ ከጋና እና ማሊ በአጠቃላይ ዘጠኝ የውጪ ተጫዋቾች በስብስቡ የያዘው ቡድኑ ከአስር ሰዓት ጀምሮ ለ90 ደቂቃዎች የቆየ ልምምዱን ነገ ጨዋታውን በሚያደርግበት ስታዲየም ሲሰራ በስፍራው ተገኝተን ታዝበናል።

ከኮቪድ ምርመራ ጋር በተያየዘ የቡድኑ አባላት ላለመስጠት ቢያንገራግሩም ምሽት ላይ ባረፉበት ሆቴል እንደሚሰጡ ሰምተናል። የቡድኑ ዝግጅት አስመልከቶ ዋና አሰልጣኙ የሰጡንን አስተያየት በተከታይነት የምናቀርብ ይሆናል።