በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ አል-ሂላል ኦምዱርማን ነገ የሚገጥመው የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በጨዋታው ዋዜማ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ያለፉትን ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በ2014 የውድድር ዘመን ቡድናቸውን በጊዜያዊነት እየመሩ ከአራት ዓመት በኋላ የሊጉን ባለ ድል ማድረጋቸው ይታወቃል። የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን የተመረጡ አሰልጣኝ ዘሪሁን ለቀጣይ የውድድር ዘመን ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ከተሾሙ በኋላ በነገው ዕለት የመጀመርያውን የነጥብ ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል። ይህን ተከትሎም በጨዋታ ዙርያ ያላቸውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።
ስለቡድኑ ዝግጅት…?
የቡድኑ አጠቃላይ ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው። ባሉን ነገሮች ሁለት ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርገናል። በዚህም የቡድናችን አጠቃላይ ሁኔታ በተለይ ብዙ ክፍተት እና የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን እንድናይ ረድቶናል። ለነገውም ጨዋታ ተዘጋጅተን በትናትናው ዕለት ባህር ዳር ገብተናል።
ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች በዝግጅት ጊዜያቸው አለመኖራቸው…?
አለመኖራቸው ትልቅ ተፅዕኖ ያደርጋል። የቡድኑ ዕድገት የት ጋር ነው ያለው ፤ መንፈሱስ ምን ይመስላል ፤ ያላቸውን መተባበር እና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ያላቸው ስሜት እኔ እንደምፈልገው ነው ወይ የሚለውን መለየት ያስችለን ነበር። በተለይ በአብዛኞቹ ዓመቱን ሙሉ ብሔራዊ ቡድን ላይ እና በፕሪምየር ሊጉ የተጫወቱ ናቸው። ይሄ ይበልጥ ጉልበታቸውን ያሳጣብሃል። ይሄም ያለውን የእርስ በእርስ መግባባት እና የምትፈልገውን ነገር ስለሚያሳጣ ትልቅ ችግር አለው።
ስለአዲስ ፈራሚዎች…?
በጣም ጥሩ ናቸው። እንዲያውም አዲስ ተጫዋቾች አይመስሉም። በጣም ተግባብተው ጥሩ ነገር እየሠሩ ነው። ያው አጥቂም ላይ ተከላካይም ላይ ከተጫዋቾቹ ጋር ያላቸው ህብረት መልካም ነው።
የአቤል እና አማኑኤል አለመኖር…?
አዎ ክፍተት አለው። አጥቂዎች ላይ አሁን ችግር አለብን። ግን ባሉን ተጫዋቾች እና ጊዮርጊስ ሲጫወት እንደ ቡድን የሚጫወት በመሆኑ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጠንክረን ሰርተናል። በሕብረት እና በአንድነት ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት በማምጣት አዲሱን ዓመት በሠላም ለመቀበል ዝግጅታችንን ጨርሰን ጨዋታውን እየጠበቅን ነው።
ስለተጋጣሚ ቡድን ስላላቸው መረጃ…?
ስለ ተጋጣሚያችንን ብዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አይተናል። ግን ብዙዎቹ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው። ባገኘነው የግል ብቃቸው እና እንቅስቃሴያቸው እንዴት ነው የሚለውን ነገር እያየን ነው። እስካሁን ድረስ በእርሱ ላይ ሠርተናል። ዘጠኝ ኢንተርናሽናል ተጫዋቾች አሏቸው ፤ ሙሉ ቡድኑ አዲስ ነው። የሱዳን ዜጋ ተጫዋቾች ጥቂት ናቸው። የግል ብቃት ያላቸው ስለሆነ እዛ ላይ ሠርተን የተሻለ ነገር ለማምጣት ዝግጅታችንን ጨርሰናል።
ከነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ…?
ጊዮርጊስ ሁሌም ሕልሙ እና ራዕዩ በአፍሪካ መድረክ የተሻለ ደረጃ መድረስ ነው። ሁሌ የአፍሪካ መድረክ ላይ ለመጫወት ነውና ሀሳባችን ከአራት ዓመታት በኋላ እዚህ መድረክ ላይ መጥተናል። አሁን የማጣሪያ ጨዋታ ነው የምንጫወተው ፤ ከባድ ጨዋታ ቢሆንም የተሻለ ቡድንን ይዘን ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ቦታው ለመመለስ ነው የምንፈልገው።