“ነገ በዓል እንደመሆኑ መጠን አሸንፈን ለደጋፊዎቻችን የበዓል ስጦታ እንሰጣቸዋለን ብለን እናስባለን” ቸርነት ጉግሳ

በዘመን መለወጫ ከሱዳኑ አል-ሂላል ኦምዱርማን ጋር ፈረሰኞቹ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት ቸርነት ጉግሳ ስለጨዋታው አስተያየቱን ሰጥቶናል።

በወላይታ ድቻ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ቸርነት ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ከመጣ ወዲህ መልካም የሚባል ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በአፍሪካ የክለቦች መድረክ የመጀመርያ ጨዋታውን ነገ ከአል-ሂላል ኦምዱርማን ጋር የሚያደርገው ቸርነት ስለዝግጅታቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

የቡድኑ ሁኔታ…?

ዝግጅታችን ከጀመርን ትንሽ ቆይተናል። እንደ ዝግጅት አሪፍ ነበር። ባሳለፍነው ጊዜ የተወሰነ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ሞክረን ራሳችንን ለማየት ችለናል። ለነገው ጨዋታም በጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ እንገኛለን።

የጨዋታ መደራረብ የፈጠረው ተፅዕኖ ስለመኖሩ…?

ባለኝ አቅም ሀገሬንም ሆነ ክለቤን ለማገልገል እየሰራሁ ነው። ምንም የፈጠረብኝ ነገር የለም። የቅድመ ዝግጅት እንደመሆኑ ብዙም ድካም የለም። ይሄ ብዙም የሚያሳስብ አይደለም።

ስለተጋጣሚያቸው…?

እንደሚታወቀው ከሱዳን ክለብ ጋር ነው ጨዋታው። ከባድ ሊሆን እንደሚችል እንገምታል። እኛ እንደ ቡድን መዘጋጀታችን ጥሩ ነገር ለማድረግ ነው። በውጤቱም ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ።

በቡድን ውስጥ ወሳኝ ተጫዋቾች ስላለመኖራቸው…?

አዎ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለ ፤ እንደ ቡድን ሊያጎድለን ይችላል። ግን ያሉን ተጫዋቾችም ጥሩ ናቸው። የእነሱ ክፍተት ይሸፈናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እግርኳስም ስለሆነ ሁላችንም ተጋግዘን ክለባችንን በሊጉ ያሳየነውን ጥንካሬ እና ውጤታማነት በዚህ መድረክ ውጤማ ጉዞ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንዳርጋለን።

ለደጋፊዎች የበዓል ስጦታ…?

ደጋፊዎቻችን ሁሌም ከጎናችን ናቸው። እነርሱን ማስደሰት እንፈልጋለን። አዎ ነገ በዓል እንደ መሆኑ መጠን አሸንፈን የበዓል ስጦታ እንሰጣቸዋለን ብለን እናስባለን። ከእግዚአብሔር ጋር ይሄ ይሳካል ብለን እናስባለን።

ያጋሩ