“አሸንፈን የበዓል ስጦታ ለደጋፊዎቻችን እንዲሁም ለቤተሰቦቻችን መስጠት እናስባለን” ቢኒያም በላይ

ከሱዳኑ አል-ሂላል ኦምዱርማን ጋር ከሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት አዲሱ የፈረሰኞቹ የመስመር አጥቂ ቢኒያም በላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ነበረው።

በተለያዮ የአውሮፓ ሀገሮች ቆይታ ካደረገ በኋላ ዳግም ወደ ሀገሩ በመመለስ በሲዳማ ቡና እና በመቻል ቆይታ ያደረገው ቢኒያም በላይ በፈረሰኞቹ ቤት የሁለት ዓመት ቆይታ ለማድረግ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ፊርማውን ማኖሩ ይታወቃል። በቡድኑ ውስጥ ፊት መስመር ላይ ያለውን መሳሳት ለመቅረፍ ታስቦ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣው ቢንያም በክለቦች የአፍሪካ መድረክ የመጀመርያ ጨዋታውን ነገ ለማድረግ እየተጠባበቀ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያም በጨዋታው ዙርያ ላነሳችለት ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።

ስለአዲሱ ክለብ ….?

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ እና ኃያል ክለብ ነው። በሊጉ ብዙ ጊዜ ዋንጫ ያነሳ ብቸኛ ክለብ ነው። ስለዚህ እዚህ ክለብ በመግባቴ ደስተኛ ነኝ ፤ በመቀጠል ከክለቡ ጋር ለመዋሃድ ያን ያህል ከብዶኛል ብዬ አላስብም። ገና ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ ታክቲካል ነገሮችን እነአዲስ እና አሰልጣኝ ዘሪሁን እየረዱኝ ነበር። ተጫዋቾቹ ብሔራዊ ቡድን አብረውኝ የተጫወቱ በመሆናቸው አልተቸገርኩም። በቅድመ ዝግጅት ደግሞ ሲምባን እና ኤል-ሜሪክን አግኝተን መጫወታችን እርስ በእርስ እንድንግባባ አድርጎናል። በአጠቃላይ በአዲሱ ክለቤ ደስተኛ ነኝ።”

ስለተጋጣሚያቸው ሂላል…?

“ አል-ሂላል ምርጥ ከሚባሉት ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ለፍፃሜ መድረስ የቻለ ነው። ይሄም ቢሆን ትልቅ ግምት እምንሰጠው አይደለም። በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ምን አይነት ኃያል ቡድን እንደሆነ ስለሚረዱት ለተጋጣሚያችን ክብር ሰጠን ከራሳችን አጨዋወት በመነሳት ለጨዋታው ተዘጋጅተናል።”

በውጭ ሀገር በመጫወት ስላለው ልምድ…?

“በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች መጫወቴ ከሀገር ውጭ የመጫወት ከፍተኛ ልምድን እንዳገኝ አድርጎኛል። ክለቤንም በዚህ ለመጥቀም አስባለው። እኔ ብቻም ሳልሆን ጊዮርጊስ ውስጥ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር የተጫወቱ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ክለባችንም ለአፍሪካ እግርኳስ እንግዳ አይደለም። የረጅም ዓመት ተሳትፎ ያለው ታሪካዊ ቡድን ነው። በጨዋታ ውስጥ የሚፈጠሩ ማንኛውንም ጫና በትዕግት ተቋቁመን አሸንፈን ለመውጣት አቅሙ አለን ብዬ አስባለው።”

ከነገው ጨዋታ ምን ይጠበቅ…?

“ይሄ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ አንድ ክለብ ፤ አንድ ቤተሰብ ነው ማለት ይቻላል። ደጋፊዎቹ ከኛ ጋር አብረው ናቸው። የክለቡ አመራሮች ከተጫዋቾች እና ከአሰልጣኞች ጋር አንድ ላይ ናቸው። የነገውን ጨዋታ የማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎት አለን ፤ ምክንያቱም በበዓል ከቤተሰቦቻችን ርቀን እዚህ ዝግጅት ላይ አሳልፈን ድጋሜ በበዓሉ ቀን ነው ምንጫወተው። ስለሆነም አሸንፈን የበዓል ስጦታ ለደጋፊዎቻችን እንዲሁም ለቤተሰቦቻችን መስጠት እናስባለን።”