በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የሱዳኑን ሀያል ክለብ አል-ሂላል የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቸርነት ጉግሳ ሁለት ግቦች ታግዘው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ድል አድርገዋል።
አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ ከሾመ በኋላ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን ለማድረግ ስታዲየም የደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ በክረምቱ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ረመዳን የሱፍ እና ቢኒያም በላይን በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ በማስገባት ጨዋታውን ቀርቧል።
ኳሱን ከሂላሎች በተሻለ በመቆጣጠር መጫወት የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ጊዮርጊሶች በዋናነት ወደ መስመር በመውጣት ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ታይቷል። ሂላሎች በአንፃሩ ቀጥተኝነት የተሞላበት አጨዋወት በመከተል የተወሰደናቸውን የኳስ ቁጥጥር አክሽፈው ፍሬያማ ለመሆን ጥረዋል። ጨዋታው 9ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን በመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም ከወደ ቀኝ ባደላ ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ቢኒያም በላይ ሲያሻማው የመስመር አጥቂው ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ ከመረብ አዋህዶት ቡድኑ መሪ ሆኗል።
ገና በጊዜ ግብ ያስተናገዱት አል-ሂላሎች በ14ኛው ደቂቃ በአጥቂያቸው መሐመድ አብደረህማን ዩሴፍ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረው የነበረ ቢሆንም አጥቂው የመታው ኳስ ለግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ እምብዛም ፈታኝ ሳይሆን መክኗል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበራቸውን ብልጫ ያጡ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በሂላሎች ቢነጠቁም ፈጣኖቹን የመስመር ተጫዋቾች በመጠቀም መሪነታቸውን ለማሳደግ ተንቀሳቅሰዋል። ሂላሎች ግን ኳሱን በመቆጣጠር እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ በመጫወት በ25ኛው ደቂቃ ከመልስ ውርወራ መነሻን ያደረገ ኳስ በመጠቀም አቻ ለመሆን ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ፈጣን አጨዋወትን መከተል የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በ30ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አሳድገዋል። በዚህም ግዙፉ አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኢሳ ፎፋና ሲመልሰው በጥሩ የቦታ አጠባበቅ ላይ የነበረው ቸርነት ጉግሳ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። በአጋማሹ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ቸርነት በ41ኛው ደቂቃም ሦስታ ለመስራት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት የመጀመሪያው አጋማሽ 2ለ0 ተገባዷል።
ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እምብዛም ሙከራዎች አልተስተዋለበትም ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸው ሂላሎች በዚህ ክፍለ ጊዜ በአንፃራዊነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ፍላጎት ሲያሳዩ ነበር። የአሠልጣኝ ዘሪሁን ተጫዋቾች በአንፃሩ በዚህ አጋማሽ በ58ኛው ደቂቃ ዳግማዊ አርዐያን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተገኑ ተሾመ ላይ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት ሔኖክ አዱኛ አሻምቶት ግብ ሊያገኙ ነበር። ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት ተጋባዦቹ በ58ኛው ደቂቃ አብዱልጀሊል አጃጉን ከርቀት ሞክሮ ሉክዋጎ በመለሰው ኳስ አደጋ ፈጥረው ተመልሰዋል።
ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት መጣራቸውን የቀጠሉት አል-ሂላሎች በ79ኛው ደቂቃ ከወደ ቀኝ በኩል ጥሩ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከደቂቃ በኋላም በተመሳሳይ መስመር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል አምርተው በጆን ካማስ ሮቢያ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። አሁንም ወደፊት መሄዳቸውን የቀጠሉት ሂላሎች በሰከንዶች ልዩነት ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህም ማካቢ ግሎዲ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት እንዲሁም የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ዕድል ሉክዋጎን ፈትኗል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና የበዛባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል በጋቶች አማካኝነት ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ጥረው ተመልሰዋል። በቀሪ ደቂቃዎች ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ፈረሰኞቹ ጨዋታውን 2ለ1 አሸንፈው ወጥተዋል።
የአል-ሂላል ኦምዱርማን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የመልስ ጨዋታ የዛሬ ሳምንት ሱዳን ላይ የሚደረግ ሲሆን የደርሶ መልስ የድምር ውጤት አሸናፊው ክለብ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ከዛለን (ደቡብ ሱዳን) እና ያንግ አፍሪካ (ታንዛኒያ) አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።