ዐፄዎቹ ለመልሱ ጨዋታ በመዲናዋ ከተማ ይዘጋጃሉ

የመጀመርያ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት ዐፄዎቹ ከቡሩንዲው ክለብ ቡማሙሩ ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ ሲዘጋጁ ይቆያል።

ባሳለፍነው ዓርብ በካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የቡሩንዲውን ክለብ ቡማሙሩ ገጥመው 3-0 በሆነ ውጤት የረቱት ፋሲል ከነማዎች የመልሱን ጨዋታ የፊታችን ዓርብ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለሁለት ቀናት ለቡድኑ አባላት ዕረፍት የሰጠው ክለቡ በዛሬው ዕለት ተጫዋቾቹ በአዲስ አበባ ዋሽግተን ሆቴል እንዲሰባሰቡ ጥሪ አድርጓል። በቀጣይ የሚጫወቱበት ሜዳ አዛም ኮምፕሌክስ ሰው ሰራሽ መሆኑን ተከትሎ ወደ ታንዛኒያ (ቡሩንዲ በካፍ ፍቃድ ያገኘ ሜዳ አለመኖሩን ተከትሎ) እስከሚያቀኑበት ጊዜ ደረስ በመዲናዋ መቀመጫቸውን በማድረግ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅታቸውን እንደሚያደርጉ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። ክለቡም 20 ተጫዋቾን በአጠቃላይ 35 የቡድን አባላት በመያዝ የፊታችን ረቡዕ ወደ ታንዛኒያ እንደሚያቀና ሰምተናል።

ዐፄዎቹ ይህንን ጨዋታ በድምር ውጤት የሚያሸንፉ ከሆነ በቀጣይ የቱኒያውን ሴፋክሲየንን እንደሚገጥሙ አስቀድሞ የወጣው መርሐ ግብር ይጠቁማል።

ያጋሩ