የቸርነት ጉግሳ ወቅታዊ የጤንነት ሁኔታ…?

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ወሳኝ ሁለት ጎሎች ትናንት ያስቆጠረውን የቸርነት የጉዳት ሁኔታ አጣርተናል።

ሀገራችንን በመወከል በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን በትናትናው ዕለት በባህር ዳር ስታዲየም ያከናወነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሱዳኑን አል-ሂላልን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወቃል። በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በመሆን ሁለቱን ወሳኝ ጎሎች ያስቆጠረው ቸርነት ጉግሳ በመጀመርያው አጋማሽ ጡንቻው ላይ ባጋጠመው ጉዳት ህክምና አግኝቶ ተመልሶ በመግባት ግልጋሎት መስጠት ችሎ እንደነበረም አስተውለናል። ተጫዋቹ ከዕረፍት መልስ ህመሙ በድጋሜ አገርሽቶበት እንደሚፈለገው ሊያንቀሳቀስው ባለመቻሉ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዶ እንደነበረም አይዘነጋም።

ወሳኙን የመልስ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ የሚያደርጉት ፈረሰኞቹ የቸርነት ጉግሳን አገልግሎት በጨዋታው ያገኛሉ ወይስ አያገኙም የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ጉዳቱ ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ እና ተጫዋቹ ለመልሱ ጨዋታ የመድረስ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የመልሱን ጨዋታ የሚያደርጉት ፈረሰኞቹ ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ በመግባት ወደ ቢሸፍቱ ይድነቃቸው አካዳሚ በማቅናት ለቀናት ሲዘጋጁ ቆይተው ወደ ሱዳን እንደሚያቀኑ አውቀናል።