ፋሲል ከነማ በነገው ዕለት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ፋሲል ከነማ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በነገው ዕለት የመጀመሪያውን የማጣሪያ መርሐግብር በባህር ዳር በደጋፊው ፊት ያከናውናል፡፡ አሰልጣኝ ኃይሉ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት እንዲሁም በተጠናቀቀው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ስንብት በኋላ የሁለተኛ ዙር ጉዞ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት መምራታቸው ይታወሳል። በዚህም ክለቡ ወጥ አቋም በማሳየት በአፍሪካ መድረክ ላይ መሳተፍ እንዲችል ሊጉን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ የቻሉት አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ በቅርቡ የዋና አሰልጣኝነት ሹመትን ካገኙ በኋላ ከሊጉ ጅማሮ በፊት በአህጉራዊ መድረክ አፄዎቹን እየመሩ በነገው ዕለት የብሩንዲውን ክለብ ቡማሙርን ያስተናግዳሉ፡፡ ከጨዋታው አስቀድሞ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኙ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡
ስለቡድኑ ዝግጅት…
ቡድናችን ሲዘጋጅ እንግዲህ አንድ ወር ከአንድ ቀን ሆኖናል። በዚህ ውስጥ ቡድኑን ለማጠናከር መካተት የነበረባቸው ልጆች አካተናል፣ በጉዳትም በቤሐራዊ ቡድንም ያልተካተቱ ነበሩ ከዛውጭ ያሉትን ግን ለኮንፌደሬሽን ዋንጫ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸውን ተጫዋቾች ይዘን ጀምረናል ከሞላ ጎደል ዝግጅታችን በጣም አሪፍ ነበር።
ስለአቋም መፈተሻ ጨዋታ…
“የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያው ጠንከር ያለ ቡድን አላገኘንም እንጂ እዚሁ ከፍተኛ ሊግ ላይ ያሉ ተጫዋቾች አንድ ላይ ተሰባስበው እነሱ ጋር አንድ ሦስት ጨዋታዎችን አድርገናል። ጠንከር ያለ ቡድን ባናገኝም
ከሞላ ጎደል ግን ጨዋታዎችን አድርገናል።”
ከቡድኑ ስለቀቁ ተጫዋቾች…
“በእርግጥ የለቀቁብን ተጫዋቾች ጠንካራ ልጆች ናቸው። እነሱን ይተካሉ ባንልም መተካት ባለብን መጠን ተክተናል። ከባለፈውም የተሻለ ነገር እንሰራለን ብለን እናስባለን።”
ስለአዲስ ፈራሚዎች…
“አዲስ ፈራሚዎች ቡድኑን እየተላመዱ ነው። አብዛኛው ተጫዋቾች በመኖራቸው ብዙ ክፍተት የለብንም። ግን የተወሰኑ ልጆች መተካት ስላለብን ቡድኑን ተቀላቅለዋል። በአጠቃላይ የመጡት ልጆች ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብለን እናምናለን።”
ስለተጋጣሚ ቡድናቸው…
“የተወሰነ ተንቀሳቃሽ ምስል ለማየት ሞክሪያለሁ። እንዲሁም ከአራት ቀን በፊት
ያደረጉት ጨዋታ ለማየት ሞክረናል ፤ ኳስ መጫወት ሚፈልግ ቡድን ነው። ከዛ ውጪ ብዙም መረጃውም የለንም። የተወሰኑ ፊልሞችን አይተናል ከዛ ተነስተን ምን ማድረግ አለብን ሚለውን ተዘጋጅተንበታል። የነገውን ጨዋታውን ነው ምንጠብቀው።”
ከቅድመ ማጣርያው ስለማለፍ…
በሁሉም አፍሪካ መድረክ ውድድሮች ሥስቱን ምክትል ሆኜ ተሳትፊያለሁ። በተወሰኑ ስህተቶች ወደ ቀጣይ ዙር ሳናልፍ ቀርተናል። ዘንድሮ ዋናው ዓላማችን ይሄን ማሳካት ነው። ባለፈው ከነበሩት ስህተቶች ላይ ተነስተን ‘አሁንስ ምን ማድረግ አለብን ?’ ብለን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የተሻለ ነገር ለማድረግ እናስባለን።”
በነገው ጨዋታ ስለማይደርሱ ተጫዋቾች…
“በጉዳት የምናጣው እንግዲህ አንድ ልጅ ብቻ ነው ፤ ሀብታሙ ተከስተን ነው። ስለዚህ ሁሉም ጤነኛ ናቸው እና በሙሉ ኃይል እንጫወታለን።”
ከደጋፊው ስለሚጠብቁት ድጋፍ…
“ምንም ጥያቄ የለውም የደጋፊው የፋሲል የጀርባ አጥንት ነው። በዚህ ሰዓት ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ከጎናችን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እነርሱንም ለማስደሰት እኛ በሚገባ ተዘጋጅተናል።”