በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ የመልስ ጨዋታውን ከቀናት በኋላ የሚያከናውነው ፋሲል ከነማ በመዲናችን አዲስ አበባ አበበ ቢቀላ ስታዲየም ልምምዱን ለመስራት ቢያስም ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል።
አስቀድመን ባጋራናቹሁ መረጃ ዐፄዎቹ የካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ የመልስ ጨዋታቸውን ወደ ታንዛንያ ከማቅናታቸው አስቀድመው ዛሬ አዲስ አበበ በመሰባሰብ ማረፊያቸውን ዋሽግተን ሆቴል በማድረግ ለሦስት ቀን ሲዘጋጁ እንደሚቆዩ ዘገበን ነበር።
በታንዛኒያ የሚጫወቱበት ሜዳ ሰው ሰራሽ መሆኑን ተከትሎ ልምምዳቸውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለማድረግ አስፈላጊውን ፍቃድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ስታዲየሙን በበላይነት ለሚያስተዳድረው የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ደብዳቤ አስገብተው ፍቃድ እንዳገኙ ተገልፆላቸው ነበር። ሆኖም ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት የቡድኑ አባላት ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ‘የተፈቀደ ነገር የለም ፤ ሜዳውን መጠቀም አትችሉም’ ተብለው መመለሳቸውን የፋሲል ከነማ ኃላፊዎች ገልፀውልናል። በምትኩም የሜዳ ለውጥ በማድረግ ሀያት ወደሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል ልምምዳቸውን ለመስራት እየተጓዙ መሆናቸውን አያይዘው አጋርተውናል።
ጉዳዩንም ለማጣራት በተደጋጋሚ ወደ ሚመለከታቸው አካላት ብንደውልም ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል።