የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ለስፖርተኞቹ ሽልማት አበረከተ

እያገባደድን ባለነው የ2014 ዓመት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ውጤት ላመጡ ስፖርተኞች የእውቅና እና የሽልማት መርሐ-ግብር ተከናወነ።

በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ገናና ስም ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበርካታ የስፖርት ዘርፎች የሚወዳደሩ ቡድኖች በስሩ ያሉት ሲሆን ክለቡም በ2014 በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤት ላመጡ ስፖርተኞች እውቅና ሰጥቷል። ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በስካይ ላይት ሆቴል በተከናወነው የእውቅና እና ሽልማት አሰጣጥ መርሐ-ግብር ላይ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና የተለያዩ የስፖርት አመራሮች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ አማን የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የእውቅና አሰጣጥ መርሐ-ግብሩ ከታዳጊ እስከ ልምድ ያላቸው ስፖርተኞች ድረስ ሽልማት መስጠትን አስከትሏል። በዚህም ለብስክሌት ቡድን አባላት ከ21 እስከ 61 ሺ፣ ለጠረቤዛ ቴኒስ ቡድን አባላት ከ16 ሺ እስከ 61 ሺ 500፣ ለአትሌቲክስ ቡድን (በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላሸነፉ) 50 ሺ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ አሸናፊዎች 30 ሺ፣ የዓለም የቤት ውስጥ አሸናፊዎች 18 ሺ፣ የአፍሪካ ውድድር አሸናፊዎች ከ10 ሺ እስከ 40 ሺ፣ የውጪ ሀገር የዓለም ሪከርድ ላሻሻሉ 75 ሺ፣ በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና አሸናፊዎች እንዲሁም ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊዎች እንደያመጡት ውጤት ከ18 ሺ ጀምሮ እስከ 300 ሺ ብር ድረስ ሽልማት ተበርክቷል።

እግር ኳስን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው ስብስብ ከ30 ሺ እስከ 61 ሺ ብር ድረስ በሽልማት መልክ ተበርክቷል። የቡድኑ አሠልጣኝ መሰረት ማኒ በአሁኑ ሰዓት ሀገር ውስጥ ባትገኝም በተወካዩዋ አማካኝነት የ230 ሺ ብር ሽልማት ተሰጥቷል። ከዋናው የሴቶች ቡድን በተጨማሪ ለታዳጊ እና ወጣቶች ቡድን አባላትም ሽልማት ተሰጥቷል።