የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው ተሹመዋል።
ኢንስትራክተር አብርሃም በአፍሪካ በኤሊት ኢንስራክተርነት ፣ በአፍሪካ ዋንጫ እና መሰል ትልልቅ ውድድሮች በቴክኒክ ጥናት ቡድን አባልነት እና አሰልጣኝነት በተጨማሪም በኤዥያ እና የመን እግር ኳስ ላይ ያላቸው የስራ ልምድ ለቦታው ተመራጭ ያደረጋቸው ሲሆን ፊፋ ለቴክኒክ ኤክስፐርትነት ያቀረባቸውን መመዘኛዎች በማለፍ እንደ ሁኔታው በሚታደስ የ2 ዓመት ኮንትራት የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በድረ-ገፁ ይፋ አድርጓል። በዚህም በፊፋ በዚህ ዘርፍ የተመረጡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ኢንስራትክተር ሆነዋል።
በፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርትነት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል በኤሊት የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ፣ በወጣቶች እግር ኳስ ፣ በግራስ ሩት ፣ ለቴክኒክ ዳይሬክተሮች ፣ ለኢንስትራክተሮች እና ከእግር ኳስ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ ኮርሶች ማዘጋጀት ፤ ለአባል ሀገራት እና አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች በእግር ኳስ ልማት ዙርያ የቴክኒክ ማማከር ፤ የአባል ሀገራት የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራሞች እና ተግባራትን መከታተል ፤ አዲሱ የፊፋ ቴክኒክ ልማት ፕሮግራም ዝግጅት እና አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ መሳተፍ እንዲሁም ሌሎች በፊፋ የቴክኒክ ልማት መምሪያ ስር የሚሰጣቸው ተግባራትን መከወን ይጠቀሳሉ።