የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና ባህር ዳር ቀጣይ ጊዜ…?

የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው እንደተሾሙ ይፋ የሆነው አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከጣና ሞገዶቹ ጋር የመቀጠላቸው ጉዳይን በተመለከተ ማጣራት አከናውነናል።

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው መሾማቸው ምሽት ላይ ይፋ መሆኑ ይታወቃል። መረጃው ይፋ ከሆነ በኋላ አሠልጣኙ ከጣና ሞገዶቹ ጋር መቀጠል እና አለመቀጠላቸው ብዙዎችን ሲያነጋግር የነበረ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን ለማጣራት ጥራ አሠልጣኙ ከክለቡ ጋር እንደማይቀጥሉ አረጋግጣለች።

በፊፋ ሀላፊነት በዓመት ውስጥ ከሦስት ወር በላይ ለሥራ ከሀገር ውጪ የሚያሳልፉት አሠልጣኙ ክለቡን መከታተያ ጊዜ ሊያጥራቸው ስለሚችል በስምምነት ውላቸውን ሊያቋርጡ እንደሆነ ተረድተናል። በአሁኑ ሰዓት በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት አዲስ አበባ የሚገኙት አሠልጣኙም ነገ ምሽት ወደ ባህር ዳር እንደሚያቀኑ የሰማን ሲሆን ከሰሞኑን ንግግር ሲያደርጉበት የነበረውን ውል የማቋረጥ ነገር መስመር ያሲዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ቢሆንም ግን አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የፊፋ ሀላፊነታቸውን እስከሚጀምሩ ድረስ ከክለቡ ጋር እንደሚቆዩ እና በቅርቡ ዋና አሠልጣኝ ተደርጎ ከሚሾመው አሠልጣኝ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ባህር ዳር ከተማ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ምትክ ለመሾም ሦስት አሠልጣኞችን በመጨረሻ ዝርዝር በመያዝ ውሳኔ ለመወሰን ማጣራት እያከናወነ እንደሆነ ሰምተናል።

ያጋሩ