የጣና ሞገዶቹ ቀጣይ አሠልጣኝ ማን ይሆን?

የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው በተሾሙት አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ምትክ ባህር ዳር ከተማዎች አዲስ አሠልጣኝ ለማግኘት ተቃርበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን 2011 ላይ የተቀላቀለው ባህር ዳር ከተማ በኮቪድ-19 ምክንያት የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ጨምሮ በአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው እና ፋሲል ተካልኝ እየተመራ ከቆየ በኋላ ሐምሌ 27 2013 ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን በ2 ዓመት ውል በመንበሩ መሾሙ ይታወቃል። ክለቡ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተመራ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን 12ኛ ደረጃን ይዞ የፈፀመ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ግን ከፍ ባለ ደረጃ ለመፎካከር በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል በመቀመጫ ከተማው ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

ቡድኑ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተመራ ይቀጥላል ቢባልም ትናንት አመሻሽ ኢንስትራክተሩ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው መመረጣቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ከቡድኑ ጋር መቀጠል እና አለመቀጠላቸውን አጣርተን ዘገባ አቅርበን ነበር። አሁን ደግሞ የእርሳቸውን ቦታ ለመተካት ከታጩ ሦስት እጩዎች መካከል አንደኛው በቦታው ለመሰየም የሰፋ ዕድል እንዳላቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አሠልጣኝ አብርሃም ከክለቡ የቦርድ አባላት ጋር በመሆን የቡድኑ ቀጣይ አሠልጣኝ እንዲሆኑ በእጩነት ካስቀመጧቸው ግለሰቦች መካከል ሥዩም ከበደ፣ ደግአረገ ይግዛው እና ሙሉጌታ ምህረት የሚገኙ መሆኑን ያወቅን ሲሆን አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ግን ከሌሎቹ በተሻለ ቦታውን ለማግኘት እጅግ ከጫፍ መድረሳቸውን የዝግጅት ክፍላችን ተረድታለች።

የቀድሞ የአውስኮድ እና ኢኮስኮ አሠልጣኝ ደግአረገ 2012 እና 2013 የውድድር ዓመትን በወልቂጤ ከተማ ያሳለፉ ሲሆን ዓምና ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሠልጣኝነት ህይወታቸውን መቀጠላቸው አይዘነጋም። አሠልጣኙ ከባንክ ጋር የአንድ ዓመት ውል ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም ውላቸው በይፋ ባለንበት መስከረም ወር የሚጠናቀቅ በመሆኑ የትውልድ ከተማቸውን ክለብ ለማገልገል ንግግር መጀመሩን አውቀናል። ምናልባት ግን እንደጠቀስነው ከባንክ ጋር ያላቸው ውል በቀናት እድሜ ስለሚቆይ ህጋዊ ስምምነቶች ይፋ የሚሆኑበት ቀን ሊገፋ የሚችል ሲሆን አልያም የቀናት ዕድሜ የቀረው የባንክ ቆይታቸው በስምምነት የሚቋጭ ከሆነ በቶሎ ክለቡን እንደሚረከቡ ሰምተናል።

ትናንት ምሽት በሰራነው ዘገባ ላይ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ አዲሱ ሀላፊነታቸውን እስከሚረከቡ ድረስ እንደ አማካሪ ሆነው አዲስ ከሚመጣው አሠልጣኝ ጋር እንደሚያገለግሉ መግለፃችን ይታወሳል።