በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል

በአማራ ባንክ ሥያሜ የሚደረገው የጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ 6 ክለቦች ሙሉ ለሙሉ ተለይተው ሲታወቁ የጅማሮ ቀንም ለውጥ ተደርጎበታል።

ዋናው የክለቦች ውድድር ከመጀመራቸው በፊት በየከተማው ከሚደረጉ ቅድመ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ በስድስት ክለቦች መካከል በባህር ዳር ከተማ እንደሚደረግ መገለፁ ይታወሳል። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገውን ውድድር ለማድመቅ ከሀገራችን ክለቦች ውጪ ሁለት ተጋባዥ የውጪ ክለቦችን እንደሚያስመጡ ከዚህ ቀደም የተገለፀ ሲሆን አሁን የውጪዎቹን ጨምሮ የሀገር ውስጥ ተሳታፊ ክለቦች ዝርዝር ሙሉ ለሙሉ መለየቱን አውቀናል።

በዚህም የዩጋንዳዎቹን ሁለት ክለቦች ቡል ኤፍ ሲ እና ሞደርን ጋዳፊን ጨምሮ ወልቂጤ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚሳተፉ ሲሆን እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በሚስጥር የተያዘው አንደኛው ተጋባዥ ክለብም ይፋ ሆኗል። በዚህም በአዲስ የእግርኳስ አጨዋወት አስተሳሰብ ብቅ ያለው ኮልፌ ተስፋ እግርኳስ ቡድን 6ኛው ክለብ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ከአዘጋጆቹ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ክለቦች ለአቋም መፈተሻ ጨዋታነት እንደሚጠቀሙት በሚታሰበው ውድድር ላይ በሰዒድ ኪያር እና ፈቀደ ትጋ አሠልጣኝነት እንዲሁም ገነነ መኩሪያ አጋዥነት የሚመራው ኮልፌ ተስፋ ቡድን የራሴ ባለው አስተሳሰብ ታዳጊዎችን እና ክለብ ያጡ ተጫዋቾችን ለማስተዋወቅ አልፎም አጨዋወቱን ለማሳየት በመፈለጉ በውድድሩ እንዲሳተፍ እንደተደረገ ተመላክቷል።

በተያያዘ መስከረም 6 እንደሚጀምር ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ይህ ውድድር መስከረም 7 የባህር ዳር ስታዲየም የኤል-ሜሪክ እና አርታ ሶላርን ጨዋታ ማስተናገዱን ተከትሎ በጨዋታው ቀን እና ከጨዋታው 24 ሰዓት በፊት ስታዲየሙ ምንም አይነት ጨዋታ እንዳያስተናግድ ስለሚከለከል እንዲሁም በኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ዩጋንዳን የወከለው ክለብ ቡል ኤፍ ሲ ቅዳሜ ጨዋታውን ስለሚያደርግ ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን በሁለት ቀናት ተገፍቶ መስከረም 8 እንዲጀመር ተወስኗል።