አዳማ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

በተከላካይ እና በአማካይ ቦታ የሚጫወቱ ሁለት ተጫዋቾች አዳማ ከተማን ተቀላቅለዋል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመሩ በ2015 የውድድር ዘመን ላይ የሚሳተፉት አዳማ ከተማዎች በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የዝግጅት ምዕራፋቸውን እየከወኑ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሙከራ ዕድል ሰጥተዋቸው የነበሩ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው አካተዋል፡፡

ታዬ ጋሻው በታዳጊ ቡድን ተጫዋችነት ወዳሳለፈው ክለብ የተመለሰበትን ዝውውር አጠናቋል፡፡ ከአዳማ ከተማ ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ አርሲ ነገሌ ቆይታ የነበረው ወጣቱ ተከላካይ ከወራት በፊት አርሲ ነገሌን ለመቀላቀል የተስማማ ቢሆንም የሙከራ ዕድል አግኝቶ ወደ ነበረበት የልጅነት ክለቡ በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል፡፡

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኤልያስ ለገሰም የክለቡ ሌላኛው አዲስ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በአምቦ ጎል ፕሮጀክት እና በኢትዮጵያ ቡና ወጣት ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው አማካዩ በሁለት ዓመት ውል አዳማን በይፋ መቀላቀል ችሏል፡፡

ክለቡ ከዚህ ቀደም በክረምቱ መስዑድ መሐመድ ፣ ዊሊያም ሰለሞን ፣ አድናን ረሻድ ፣ ቦና ዓሊ ፣ ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ክዋሜ ባህ እና ፍሬድሪክ አንሳህን ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡