ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የቻን ውድድር የምድብ እጣ ማውጣት መርሐ-ግብር የሚከናወንበት ቀን ተገልጿል።
በ2023 በአልጄሪ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የቻን ውድድር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳታፊዎችን ቁጥር አሳድጎ በ18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ከጥር 5 -27 ድረስ እንደሚከናወን ይታወቃል። በየቀጠናው በተከናወኑ የማጣሪያ ውድድሮች ሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ጋና፣ አይቮሪኮስት፣ ኮንጎ፣ ዲ አር ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ማዳጋስካር፣ አንጎላ እና ሞዛምቢክ አልፈው ከአዘጋጇ ሀገር አልጄሪያ ጋር በመሆን ውድድራቸውን ለማድረግ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
አሁን ይፋ በሆነ መረጃ መሠረት ደግሞ ጥር ላይ ለሚጀምረው ውድድር መስከረም 21 በአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ የምድብ ድልድል እንደሚወጣ ተመላክቷል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያ ጨዋታዎች የደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ አቻውን ገጥሞ አንድም ግብ ሳያስተናግድ በተቃራኒው 6 ግቦችን አስቆጥሮ ወደ መድረኩ ከ2016 በኋላ የተመለሰበትን ውጤት ማግኘቱ ይታወሳል።