በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ላይ ተካፋይ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአል-ሂላል ጋር ያለበትን የመልስ ጨዋታ ሱማሌያዊያን ዳኞች እንደሚመሩት ተገልጿል።
በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ሀገራችንን በመወከል ፈረሰኞቹ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑም የሱዳኑን ክለብ አል-ሂላልን በማጣሪያው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ባህርዳር ላይ አስተናግዶ 2ለ1 ማሸነፍ የቻለው ሲሆን የመልሱን መርሐ-ግብር ሱዳን ኦምዱርማን ላይ የፊታችን ሰኞ መስከረም 9 ላይ ያከናውናል፡፡ ይህንን ጨዋታ እንዲመሩ ካፍ አራት የሱማሌያ ዜግነት ያላቸውን ዳኞች መመደቡም ይፋ ሆኗል።
ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የ29 ዓመቱ ዑማር አብዱልቃድር አርታን ሲመሩት በረዳትነት ዳኝነት ሀምዛ ሀጂ እና ዓሊ መሐመድ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ሀሰን መሐመድ መመደባቸው ተመላክቷል። የሊቢያ ዜግነት ያላቸው ጋማል ሳሊ በበኩላቸው የጨዋታው ታዛቢ በመሆን ሆነዋል።