አዳማ ከተማ ረዳት አሠልጣኝ ሾሟል

በአሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመሩ በባቱ ከተማ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ረዳት አሰልጣኝ ሲቀጥሩ አምስት ወጣቶችንም ከታዳጊ ቡድናቸው አሳድገዋል፡፡

ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ይፋዊ ሹመት በኋላ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማጣመር በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው አዳማ ከተማ በዛሬው ዕለት በይፋ ረዳት አሰልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን ይሁንታ አግኝቶ የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው ተረፋ ሂርጳሳ ነው፡፡ በኦሮምያ ፓሊስ ውስጥ የተጫዋችነት ዘመኑን ያሳለፈው እና በከፍተኛ ሊጉ ገላን ከተማን ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለው አሰልጣኙ ቀጣዩን የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ብቅ በማለት የአዳማ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ግልጋሎት ይሰጣል።

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎች እና ከነባር ተጫዋቾች ውል ማራዘም በኋላ ፊቱን ወደ ታዳጊ ቡድኑ በማዞር ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አምስት ተጫዋቾችን አሳድጓል፡፡ በተከላካይ ቦታ ላይ አብዲ ዋበላ እና ፉዐድ ኢብራሂም ፣ በአማካይ ስፍራ ጋዲሳ ዋዶ እና ሳዲቅ ዳሪ እንዲሁም በአጥቂ ቦታ አብዱልፈታህ ሰፋህ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻሉ ተጫዋቾች መሆናቸው ተመላክቷል።