በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ወደ ባህር ዳር መግባት ጀምረዋል

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ወደ ውድድሩ ስፍራ መግባት ሲጀምሩ የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊም ነገ ኢትዮጵያ ይደርሳል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ አማካኝነት የሚዘጋጀው የመጀመሪያው የጣና ዋንጫ ውድድር በአማራ ባንክ ሥያሜ ከመስከረም 8 ጀምሮ እንደሚካሄድ ይታወቃል። በውድድሩ ላይም ባህር ዳር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ኮልፌ ተስፋ፣ ቡል ኤፍ ሲ እና ሞደርን ጋዳፊ እንደሚሳተፉ ይፋ መሆኑን ገልፀን ነበር። እነዚህ ተሳታፊ ክለቦችም ከትናንት ጀምሮ ወደ ውድድሩ ስፍራ ባህር ዳር ከተማ እያቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የውድድሩ ስፍራ ቀድሞ የደረሰው ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ሲሆን እሁድ ጨዋታዎቹ እስከሚጀምሩ ዝግጅቱን እዛው እያደረገ እንደሚጠባበቅ ተጠቁሟል። የውድድሩ አዘጋጅ ከተማ ክለብ ባህር ዳር ከተማ እዛው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኝ ሲሆን ሌላኛው የሊጉ ክለብ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከነገ በስትያ ወደ ስፍራው እንደሚያመራ ተጠቁሟል። በራሱ የአጨዋወት አስተሳሰብ ብቅ እንዳለ የሚገልፀውና በሰዒድ ኪያር እንዲሁም ፈቀደ ትጋ አሠልጣኝነት የሚመራው ኮልፌ ተስፋ ክለብ በበኩሉ በውድድሩ ጅማሮ ዋዜማ ቅዳሜ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ውድድሩን ለማድመቅ ከውጪ በተጋባዥነት እንዲሳተፉ የተደረጉት የዩጋንዳዎቹ ሞደርን ጋዳፊ እንዲሁም ቡል ኤፍ ሲ’ም የቪዛ እና የትኬት ጉዳዮችን እንዳገባደዱ ከውድድሩ አዘጋጆች መረጃ ደርሶናል።

2017 ላይ የተመሰረተው እና በቅርቡ በስፖንሰር አማካኝነት ስሙን ሞደርን ጋዳፊ ብሎ የቀየረው ክለብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመስርቶ በዩጋንዳ የሊግ እርከኖች አልፎ በዋናው ፕሪምየር ሊግ ላይ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በተጠናቀቀው የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግም 8ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በቅርቡ ከሀገራችን ተቋም ጎፈሬ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት እንደፈፀመ የሚታወቀው ክለቡም ለአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ነገ ወደ ሀገራችን እንደሚገባ ተረጋግጧል።

ሁለተኛው የዩጋንዳ ክለብ ቡል ኤፍ ሲ’ም እንደ ሞደርን ከቀናት በፊት ከጎፈሬ ጋር የትጥቅ ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የሀገራችንን ምርት እየተጠቀመ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ከግብፁ ክለብ ፊውቸር ኤፍ ሲ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን አከናውኖ ያለ ግብ የተለያየው ክለቡም በዛሬው ዕለት የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ካይሮ የደረሰ ሲሆን ቅዳሜ የመልሱን ጨዋታ አከናውኖ በቀጥታ እሁድ ለሊት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ተብሏል።

የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ከመስከረም 8 እስከ 14 ድረስ በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚከናወን ይታወቃል።

ያጋሩ